የኢራን ፕሬዝዳንት አሜሪካ ቴህራንን “የማተራመስ ፖሊሲ” እየተገበረች ነው ሲሉ ከሰሱ
አያቶላ አሊ ካሜኒ በበኩላቸው “በረብሻው የአሜሪካ እጅ መኖሩ የሚያመላክቱ ማስረጃዎች በግልጽ እየታዩ ነው” ብለዋል
አሜሪካ፤ ኢራናውያን በነጻነት ተቃውሞ የማድረግ መብታቸው ሊከብርላቸው ይገባል እያለች
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ አሜሪካ በሀገሪቱ የተነሳውን ተቃውሞ ሽፋን በማድረግ ቴህራንን “የማተራመስ ፖሊሲ” እየተገበረች ነው ሲሉ ከሰሱ፡፡
የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ነው።
የማህሳ አሚኒ ሞት ታዲያ በ16 ኢራን ከተሞች ላይ ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ማዕበል ቀስቅሷል።
በኢራን ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደረገው የሚታዩት አያቶላ አሊ ካሜኒ እንደዚህ አይነት ተቃውሞ ሲገጥማቸው በኢራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
በዚህ የተደናገጠው የሀገሪቱ መንግስትም ታዲያ ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው ባላቸው 100 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ የሀገሪቱ ዓቃቤ ህግ አስታወቋል፡፡
የኢራን መሪዎች ግን ለተቀሰቀቀሰው ማዕበል ዋሽንግተንን ተጠያቂ ያደረጉ ይመስላል፡፡
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በካዛክስታን በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር "አሜሪካ በወታደራዊ ኃይል ውድቀት እና ማዕቀብ ሽንፈትን ተከትሎ ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ተሞክሮ የወደቀውን የማተራመስ ፖሊሲ በመተግበር ላይ ናቸው" ሲሉ መደመጣቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2018 የወቅቱ የአሜሪከው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ሀገራቸውን በኢራን እና በዓለም ኃያላን መንግስታት መካከል ከተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ዋሽንግተን በቴህራን ላይ ተከታታይ ማዕቀቦችን ጥለች።
ራይሲ"የኢራን በውስጥ ጥንካሬዋ ላይ የተመሰረተ እድገት ማስመዝገብ ኃያላኖቹ ድንጋጤ ፈጥሮባቿል " ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢራን መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ በበኩላቸው የእስላማዊ ሪፐብሊክ ቀንደኛ ጠላቶች አሜሪካና እና እስራኤል “ሁከትና ብጥብጥ” እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
"ዛሬ፤ ሁሉም ሰው በእነዚህ የጎዳና ላይ ረብሻዎች ውስጥ የጠላቶችን ተሳትፎ መኖሩ ያረጋግጣል"ም ብለዋል አያቶላ አሊ ካሜኒ ፡፡
"እንደ ፕሮፓጋንዳ፣ በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መሞከር፣ ደስታን መፍጠር፣ ማበረታታት አልፎ ተርፎም ተቀጣጣይ ቁሶችን ማምረትን የመሳሰሉ የጠላት ድርጊቶች አሁን ሙሉ በሙሉ ግልጽ ሆነዋል" ሲሉም አክሏል።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በሰባት የኢራን ባለስልጣናት ላይ ተቃውሞ “አፍነዋል” በሚል ማዕቀብ ጥላለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደርም፤ የኢራን ባለስልጣናትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ እና ኢራናውያን በነጻነት ተቃውሞ እንዲያደርጉ መብታቸውን እንደሚደግፍ በግልጽ ተናግሯል ።
የማህሳ አሚኒ ሞት ተከትሎ በኢራን የተቀሰቀሰው ከባድ ተቃውሞ የኢራን መንግስት ቴሌቭዥን እስከመጥለፍ የደረሰ ድርጊት የተስተዋለበትም ጭምር መሆኑም ይታወቃል፡፡
ከቀናት በፊት የተከናወነው የቴሌቭዥን መጥለፍ ድርጊት በመተላለፍ ላይ የነበረውን ዜና በማቋረጥ በሀገሪቱ መሪ ላይ የተነሳው ተቃውሞ የሚያሳዩ ምስሎች የተላለፈበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከበስተጀርባ በሙዚቃ በታጀበው ተቃውሞ “ጂን ፣ጂያን ፣አዛዲ” ትርጉሙ “ሴት ፣ህይወት ፣ነጻነት” የሚል መፈክር ሲሰማ እንደነበርም ኢራን ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡
ቀጥሎም በስክሪኑ ላይ ጭንብል ከታየ በኋላ የኢራኑ ታላቁ መሪ አሊ ካሜኒ ጭንቅላታቸው በሽጉጥ ኢላማ ሲደረግና ምስላቸው በእሳት ነበልባል ሲያዝ የታየበትም ነበር፡፡
ለጥቂት ሴኮንዶች በቆየው የጠለፋ ድረጊት የማህሳና በቅርብ በነበረው ተቃውሞ የተገደሉ ሶስት ሴቶችንም ምስሎች የተላለፉበት እንደነበርም ተገልጸዋል።
በፎቶው ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች አንዱ “ተቀላቀሉን እና ተነሱ” የሚሉ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “የወጣቶቻችን ደም ከመዳፋችሁ ላይ ይንጠባጠባል” የሚሉ ናቸው።
ድረጊቱ የፈጸመው ራሱን “አዳላት አሊ” ወይም “አሊ ዳኛ” ተብሎ የሚታወቀው የአክቲቪስቶች ቡድን ነው፡፡
ለጠላፋው ኃላፊነት እንደሚወስድ በግልጽ ያስታወቀው ቡድኑ፤ ጠለፋውን “ጣፋጭ ወቅት” በማለት የቲዊተር ተጠቃሚዎች የጠለፋውን ምርጥ ትውስታ እንዲልኩ ማበረታታቱንም አይዘነጋም።