አያቶላ አሊ ካሜኒ እንደዚህ አይነት ተቃውሞ ሲገጥማቸው በኢራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
ኢራን ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው ባለቻቸው 100 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቷ ተገለጸ፡፡
የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ነው።
የማህሳ አሚኒ ሞት ታዲያ በኢራን ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ማዕበል ቀስቅሷል።
በኢራን ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደረገው የሚታዩት አያቶላ አሊ ካሜኒ እንደዚህ አይነት ተቃውሞ ሲገጥማቸው በኢራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
በዚህ የተደናገጠው የሀገሪቱ መንግስትም ታዲያ ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው ባላቸው 100 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ የሀገሪቱ ዓቃቤ ህግ አስታወቋል፡፡
“ሁከት ፈጣሪዎች” ላይ ፈጣን ፍርድ ለመስጠት ቃል ገብቷል ዓቃቤ ህግ።
የቴህራን ግዛት 60 ክሶችን ሲይዝ 65ቱ ሰዎች ደግሞ በደቡባዊ ሆርሞዝጋን ግዛት ለተፈጠረው " ሁከት" ተጠያቂ ናቸው በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል ዘግቧል።
የሆርሞዝጋን ዋና ዳኛ ሞጅታባ ጋህሬማኒ “ሁከት ፈጣሪዎቹ ህገወጥ ስብሰባዎችን በማደራጀት፣ በህዝብና የግል ንብረት በማቃጠል፣ በህዝብ ላይ ሽብር በመዝራት ትልቁን ሚና በመጫወታቸው፣ አቃቤ ህጉ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ፈጣን ምርመራ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።
በኢራን የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተከትሎ በሆርሞዝጋን 88 ተቃዋሚዎች እና ወደ 1ሺህ 200 የሚጠጉ ተጨማሪ 60 ሴቶች በሰሜን ግዛቶች መታሰራቸውን የኢራን መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
የቴህራን ዓቃቤ ህግ አሊ ሳሊሂ ለሚዛን ኦንላይን እንደተናገሩት” ከአሁን ጀምሮ የሰዎችን ህይወት ወይም ንብረት፣ወታደር ወይም የከተማ መሰረተ ልማት የሚያጠቁ ወይም ሰዎችን ወደ አመጽ የሚያነሳሱ ወይም የሚያበረታቱ አካላት ላይ ፖሊስ ቆራጥ እርምጃ ይወሰድባቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የማህሳ አሚኒ ሞት ተከትሎ በኢራን የተቀሰቀሰው ከባድ ተቃውሞ የኢራን መንግስት ቴሌቭዥን እስከመጥለፍ የደረሰ ድርጊት የተስተዋለበትም ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከቀናት በፊት የተከናወነው የቴሌቭዥን መጥለፍ ድርጊት በመተላለፍ ላይ የነበረውን ዜና በማቋረጥ በሀገሪቱ መሪ ላይ የተነሳው ተቃውሞ የሚያሳዩ ምስሎች የተላለፈበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከበስተጀርባ በሙዚቃ በታጀበው ተቃውሞ “ጂን ፣ጂያን ፣አዛዲ” ትርጉሙ “ሴት ፣ህይወት ፣ነጻነት” የሚል መፈክር ሲሰማ እንደነበርም ኢራን ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡
ቀጥሎም በስክሪኑ ላይ ጭንብል ከታየ በኋላ የኢራኑ ታላቁ መሪ አሊ ካሜኒ ጭንቅላታቸው በሽጉጥ ኢላማ ሲደረግና ምስላቸው በእሳት ነበልባል ሲያዝ የታየበትም ነበር፡፡
ለጥቂት ሴኮንዶች በቆየው የጠለፋ ድረጊት የማህሳና በቅርብ በነበረው ተቃውሞ የተገደሉ ሶስት ሴቶችንም ምስሎች የተላለፉበት እንደነበርም ተገልጸዋል።
በፎቶው ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች አንዱ “ተቀላቀሉን እና ተነሱ” የሚሉ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “የወጣቶቻችን ደም ከመዳፋችሁ ላይ ይንጠባጠባል” የሚሉ ናቸው።
ድረጊቱ የፈጸመው ራሱን “አዳላት አሊ” ወይም “አሊ ዳኛ” ተብሎ የሚታወቀው የአክቲቪስቶች ቡድን ነው፡፡
ለጠላፋው ኃላፊነት እንደሚወስድ በግልጽ ያስታወቀው ቡድኑ፤ ጠለፋውን “ጣፋጭ ወቅት” በማለት የቲዊተር ተጠቃሚዎች የጠለፋውን ምርጥ ትውስታ እንዲልኩ ማበረታታቱንም አይዘነጋም።