የቀድሞው የብሄራዊ ደህንነት ሃላፊ የሃይማኖታዊ መሪው አሊ ሃሚኒ ታማኝ ሰው እንደነበሩ ተነግሯል
ኢራን ለረጅም አመታት ያገለገሉትን የሀገሪቱን የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ዋና ጸሃፊ ከስልጣን አነሳች።
ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሀገሪቱ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳይ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸውን አሊ ሻምክሃኒ ከስልጣን ማንሳታቸውን የኢራን ብሄራዊ የዜና ወኪል (ኢርና) ዘግቧል።
በምትካቸውም የ62 አመቱ አሊ አክባር አህመዲን ተሹመዋል ነው የተባለው።
አህመዲን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ፓራኮማንዶ ሃይል አዛዥ እንደነበሩ ተነግሯል።
የቀድሞው የደህንነት ሹም ሻምክሃኒ በቅርቡ ስማቸው ከሙስና ወንጀል ጋር ሲነሳ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ኢራን በ2015 ከምዕራባውያን ጋር በደረሰችው የኒዩክሌር ስምምነት ላይ አሻራቸውን በጉልህ ያኖሩት አሊ ሻምክሃኒ፥ ለኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አሊ ሃሚኒ ታማኝ ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል ይጠቀሳሉ።
በቅርቡም ኢራን ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ግንኙነቷን ለማደስ በቻይና በደረሰችው ስምምነት የደህንነት ሹሙ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸውን የደህንነት ሃላፊ ከስልጣን ያነሱበት ምክንያት ባይጠቀስም ከሙስና ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገምቷል።
ከሻምክሃኒ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የብሪታንያ እና ኢራን ጥምር ዜግነት ያለው አሊ ሬዛ አክባሪ በጥር ወር 2023 በቁጥጥር ስር ውሎ በስለላ ወንጀል መከሰሱ ይታወሳል።
የደህንነት ሃላፊው ከአክባሪ ጋር አደረጉት በስልክ አደረጉት የተባለው ንግግርም መለቀቁ አይዘነጋም።
ሻምክሃኒ ግን ከሙስና ጋር ተያይዞ የሚቀርብባቸውን ክስ እንደማይቀበሉት በተደጋጋሚ ገልጸዋል።