ቻይና ሁለቱን የመካከለኛው ምስራቅ ባላንጣ ሀገራት ማስታረቋ ይታወሳል
ሳኡዲ አረቢያ እና ኢራን ባለፈው ሳምንት ሻክሮ የቆየውን ዲፕሎማሲዊ ግንኙነታቸው ለማሻሻል ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ሁለቱም የመካከለኛው ምስራቅ ኃያላን ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማደስ የተስማሙት ቻይና ባደረገችው ስኬታማ የማስታረቅ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ስምምነቱን ተከትሎም የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ሪያድን እንዲጎበኙ ከሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሳልማን ግብዣ እንደቀረበላቸው ሮይተርስ የኢራን ባለስልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ መሀመድ ጃምሺዲ “ ለፕሬዝዳንት ራይሲ በተጻፈው ደብዳቤ… የሳኡዲ አረቢያው ንጉስ በሁለቱ ወንድማማች ሀገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት በደስታ መቀበላቸውን ገልጸው ራይሲ ሪያድን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበውላቸዋል" ብለዋል፡፡
ከሳኡዲ ጋር ያለው ግንኙነት ወደነበረበት እንዲመለስ ከፍተኛ ፍላገት ያላቸው ፕሬዝዳንት ራይሲ ግብዣውን እንደተቀበሉትም መሀመድ ሻምሺዲ ገልጸዋል፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂን በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ዲፕሎማቶቻቸው መካከል ስብሰባ ለማድረግ መስማማተቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሚኒስተሩ ስብሰባው የሚካሄደው መች እና የት ነው ለሚለው ግን በግልጽ ያሉት ነገር የለም፡፡
ሪያድ እና ቴህራን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሁለት ወራት ውስጥ ኤምባሲዎቻቸውን በመክፈት የንግድ እና የደህንነት ትብብር እንደሚጀመሩም አስታውቀዋል።
የሳኡዲ እና የኢራን ግንኙነት መሻከር የጀመረው ከሰባት አመታት በፊት ሳኡዲ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል ባለቻቸው በታዋቂው የሺአ ሙስሊም መሪ ሼክ ኒምር አል-ኒምርን ላይ የሞት ፍርድ መበየኗን ተከትሎ እንደነበር ይታወሳል።
በተለይ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በቴህራን የሚገኘውን የሳኡዲ ኤምባሲ ጥሰው የገቡበት አጋጣሚ ሪያድና ቴህራን በይፋ መካሰስ የጀመሩበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህ ብቻ አልነበረም ሀገራቱ በየመን እና በሶሪያ ጦርነቶች በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ተፋላሚ ኃይሎችን በመደገፍ በእጅ አዙር ሲፋለሙ ቆይተዋል።
ከአመታት የእርስ በርስ መካሰስ በኋላ ሀገራቱ አሁን ላይ በጠርጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር መስማማታቸው ትልቅ እርምጃ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
ስምምነቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት በበጎ መልኩ እንደሚመለከቱት እየገለጹ ይገኛሉ።
የሳኡዱ እና ኢራን ወደ ጤናማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መምጣት የቀጠናውን ፖለቲካ ከመቀየር አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን ፤የሳኡዱ አጋር ከሆነችው ባህሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል እንድምትፈልግ አስታውቃለች፡፡
የሳኡዲ እና ኢራን ግንኙነት መጀመር በበጎ የተቀበለችው ባህሬን በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር የለም ተብሏል፡፡
ቴህራን ከሳኡዲ እና ባህሬን በተጨማሪ በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሻሻል እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡