ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጀርመን ጉብኝት ሲያደርጉ ያለማንም ፍቃድ ጥቃቱን እንፈጽማለን ማለታቸው ተገልጿል
እስራኤል በባላንጣዋ ኢራን ላይ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማሳሰቧን ቀጥላለች።
ከሰሞኑ በጀርመንግ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም “የኢራንን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት ለማስቆም የሚያግደን ሃይል የለም” ማለታቸውተገልጿል።
ተንታኞችም ኔታንያሁ “እርምጃ ለመውሰድ የሚያግደን ሃይል የለም” ማለታቸውን ያለአሜሪካ እውቅና በቴህራን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈጸም እንችላለን እንደማለት ቆጥረውታል።
ቴህራንን ከ”ናዚ” ጋር ያመሳሰሉት ኔታንያሁ “ሁለተኛውን የዘር ፍጅት” መፍቀድ የለብንም ያሉ ሲሆን፥ ለአያቶላዎቹም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ልከዋል።
አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣን ለኢራን ኢንተርናሽናል እንደተናገሩት፥ የኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራም በእስራኤል የስለላ ድርጅት አማካኝነት ለሰባት አመት ተጓቷል።
አሁን ላይ ግን ቴህራን ቀይ መስመሩን መርገጥ ጀምራለች ያሉት ባለስልጣኑ፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአውሮፓ ሀገራት ጉብኝትም ይህንኑ እውነት ለማስረዳትና ለቴህራንም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለመስደድ ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኔታንያሁ በበርሊን ቆይታቸው ለመራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ሀገራቸው ያለአሜሪካ ይሁንታ በኢራን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ማድረስ እንደምትችል አስረግጠው ነግረዋቸዋልም ነው ያሉት።
ሹልዝም የእስራኤልን ደህንነት ማስጠበቅ ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ውስጥ ከፊት የሚቀመጥ ነው ብለዋል።
የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ በበኩሉ “ኔታንያሁበኢራን ላይ ያልሰነዘሩት ዛቻ የለም፤ የለመድነው ነገር ነው፤ ከቃላት ጦርነት ውጭ የሚመጣ ለውጥ የለም” የሚል ትዝብቱን አስቀምጧል።
ጋዜጣው የኢራን የኒዩክሌር ጣቢያዎች በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ መሆናቸው ለቴል አቪቭ ይዞት የሚመጣውን አደጋም ያነሳል።
በኢራቅ በፈረንጆቹ 1981 እንዲሁም በሶሪያ በ2007 በማብለያዎች ላይ እንደተፈጸመው ጥቃት ቀላል እንደማይሆን በማከል።
ከአሜሪካ ጋር ተቀራርቦና ተናቦ መስራት ካልተቻለም የሚፈለገው ውጤት አይመጣም ብሏል ሃሬትዝ ጋዜጣ።
የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሃላፊው ዛቺ ሃንግቢ ግን የኔታንያሁ የዚህ ምርጫ ዘመን ዋነኛው ትኩረት የኢራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ማፈራረስ ነው ማለታቸውን ቻናል 12 ዘግቧል።
“የኒዩክሌር ድርድሩ በስምምነት ካልተቋጨና አሜሪካ ገለልተኛ እርምጃ የማትወስድ ከሆነ ኔታንያሁ የኒዩክሌር ጣቢያዎቹንያፈራርሳቸዋል”ም ነው ያሉት።
በበርሊን ጉብኝታቸው ወደ ቴህራን የማስጠንቀቂያ መልዕክት የሰደዱት ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደዛቱት የቴህራንን የኒዩክሌር ማበለያዎች ያወድማሉ ወይ የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።