የኢራን ኮማንዶ ጦር ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት ያላትን መርከብ ያዘ
የፖርቹጋል ሰንደቅአላማ የሰቀለችው መርከቧ ከአረብ ኢምሬትስ ወደብ ተነስታ ወደ ህንድ እያቀናች ነበር ተብሏል
በእስራኤል እና ኢራን መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በዚህ ወቅት የኢራን ጦር በሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ አቅራቢ እቃ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር አውለዋል
የኢራን ኮማንዶ ጦር ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት ያላትን መርከብ ያዘ።
እስራኤል አድርሳዋለች በተባለው የደማስቆ የኢራን ኢምባሲ ጥቃት ምክንያት በእስራኤል እና ኢራን መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በዚህ ወቅት የኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ኮማንዶዎች በሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ አቅራቢ እቃ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ስር አውለዋል።
መርከቧን በቁጥጥር ስር ያዋላት በሶሪያ በደረሰው ጥቃት ሁለት ጀነራሎቹን ያጣው የኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ነው ተብሏል።
ኤምኤስሲ አሪየስ የተሰኘችው መርከቧ አሁን ወደ ኢራን የውሃ ክልል እየተጓዘች መሆኗን ሮይተርስ የኢራኑን የመንግስት ዜና አገልግሎት አይአርኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
የፖርቹጋል ሰንደቅአላማ የሰቀለችው መርከቧ ከአረብ ኢምሬትስ ወደብ ተነስታ ወደ ህንድ እያቀናች ነበር ተብሏል።
እንደዘገባው ከሆነ መርከቧ በእስራኤላዊው ቢሊየነር ኢያል ኦፈር እና ቤተሰቦቹ የሚመራው ዞዲያክ ግሩፕ አካል ከሆነው እና መቀመጫውን ለንደን ካደረገው ዞዲያክ ማሪታይም ጋር ግንኙነት አላት።
ኤፒ አገኘሁት ያለው የቪዲዮ ማስረጃ ወታደሮች ከሄሊኮፕተር ወርደው መርከቧን ሲይዙ ያሳያል።
ዞዲያክ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የጣሊያን እና የስዊድን ሺፒንግ ቡድን የሆነው ኤምኤስሲ ለመርከቧ እንቅስቃሴ ኃላፊት እንደሚወስድ ገልጿል።
ኤምኤስሲ በመርከቧ ላይ 25 ሰራተኞች እንደነበሩ አረጋግጦ፣ ሁሉም በሰላም እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታውቋል።
ኢራን በኢምባሲዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን እንደምትበቀል መግለጿን ተከትሎ አሜሪካ እና እስራኤል ስጋት ውስጥ ገብተዋል።
የጥቃቱን አይቀሬነት የገለጸችው አሜሪካ ተጨማሪ ኃይል ወደ መካከለኛው ምስራቅ አሰማርታለች።