ኢራን ጆርዳን ከእስራኤል ጋር የምትተባበር ከሆነ ልታጠቃ እንደምትችል አስጠነቀቀች
ኢራን በሶሪያ ለደረሰባት የእስራኤል ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች
ጆርዳን ወደ አየር ክልሏ የገቡ የኢራን ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች
ኢራን ጆርዳን ከእስራኤል ጋር የምትተባበር ከሆነ ልታጠቃ እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡
እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኝ የኢራን ኢምባሲ ላይ ባደረሰችው የአየር ላይ ጥቃት ሁለት ወታደራዊ አዛዦችን ጨምሮ ዘጠኝ ኢራናዊያን መገደላቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ በኢምባሲዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን እንደምትበቀል ስትዝት የቆየችው ኢራን መጠነ ሰፊ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃት ወደ ቴልአቪቭ መተኮሷን አስታውቃለች።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ወደ እስራኤል ድንበር በርካታ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን መተኮሱን አስታውቋል።
ወደ እስራኤል ከተተኮሱት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል የጆርዳን ጦር የተወሰኑትን መትቶ እንደጣለ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህ ድርጊት የተበሳጨችው ኢራንም ጆርዳን ከእስራኤል ጎን የምትቆም ከሆነ ልታጠቃት እንደምትችል አስጠንቅቃለች፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ለጆርዳን መረጃ አጋርታ እና አሳውቃ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ጆርዳን ግን የአየር ክልሏን ዝግ ማድረጓ ተገልጿል፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት መጀመሯን አስታወቀች
ኢራን ጆርዳንን ጨምሮ ሌሎች የእስራኤል ጎረቤት ሀገራትን ገለልተኛ እንዲሆኑ አስጠንቅቃለች ተብሏል፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ ስላደረሰችው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ጉዳት እስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ የሌለ ሲሆን እስራኤል ግን ከአሜሪካ እና ሌሎች አጋር ሀገራት ጋር በመተባበር የተቃጣባትን ጥቃት ማክሸፏን አስታውቃለች፡፡
በጆርዳን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች ያሉ ሲሆን ከዚህ በፊት በኢራን ይደገፋሉ የተባሉ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሶስት ወታደሮች ሲገደሉ ቁጥራቸው እስካሁን ያልተገለጹ ደግሞ እንደቆሰሉ ተገልጾ ነበር፡፡
የኢራን-እስራኤል ጥቃትን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከፍተኛ የተባለ ውጥረት የተከሰተ ሲሆን በረራዎች ሙሉ ለሙሉ ታግደዋል፡፡