ሚሳኤሎች በመካከለኛው ምስራቅ የጉልበት መለካኪያ ሆነዋል
የወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች እያደገ መምጣት ጦርነቶች ከቀጥተኛ የእግረኛ ጦር ፍትጊያ ወጥተው ሰው አልባ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲያውሉ አድርጓል፡፡
በቀጠናው በተለይም በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ ሄዝቦላህ ፣ ሁቲ እና የሃማስ ታጣቂዎች የርቀት መጠናቸው የተለያዩ ሚሳኤል እና ሮኬቶችን ታጥቀዋል፡፡
እነዚህን ቡድኖች በማስታጠቅ እና በመደገፍ ዋነኛ ተዋናይ የሆነችው ኢራን በበኩሏ በአሜሪካ እና በመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀብም ውስጥ ሆና የሚሳኤል ቴክኖሎጂዎቿን ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች፡፡
ቀጠናዊ ውጥረቱ ባየለበት መካከለኛው ምስራቅ ሚሳኤል እና ሮኬቶች የጉልበት መለካኪያ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
ከ3000 በላይ ሚሳኤሎች እንዳሏት የሚነገርላት ቴሄራን የባለስቲክ ፣ የሀይፐርሶኒክ እና ክሩዝ ሚሳኤሎች ባለቤት ናት።
እነዚህ ሚሳኤሎች በአየር ላይ በመተጣጠፍ ለአየር መቃወሚያዎች አስቸጋሪ በመሆን ፣ ኢላማቸውን በትክክል በመምታት ፣ በሚሸከሙት የጦር አረር እና በሚያካልሉት ርቀት የተለያዩ ናቸው፡፡
ሀገሪቷ የታጠቀቻቸው ባላስቲክ ሚሳኤሎች ከምድር ከባቢ አየር ውጭ በመውጣት ወደ ኢላማቸው በቀጥታ የመምዘግዘግ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ዲፌንስ ኢንተለጄንስ ኤጄንሲ ባወጣው መረጃ የቴሄራን ባለስቲክ ሚሳኤሎች ከ300 – 2400 ኪሎ ሜትሮችን የመምዘግዘግ አቅም አላቸው ይላል።
ከነዚህ ውስጥ “ሻሀብ- 3” የተባለውን እስከ 2 ሺህ ኪሎሜትር የሚወነጨፈው ሚሳኤል አንዱ ሲሆን ከ760 -1200 ኪሎግራም ድረስ የሚመዝን የጦር አረር ይሸከማል፡፡
በተጨማሪም ሻሀብ -1 ፣ ፋታህ ፣ ሻሀብ -2 ፣ ዞልፍዘሀር እና ኪያም የተባሉ እስከ 1750 ኪሜ ድረስ የሚወነጨፉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በጦሯ ውስጥ አካታለች፡፡
ኢራን ከባለስቲክ ሚሳኤሎች በተጨማሪ የሀይፐርሶኒክ እና ክሩዝ ሚሳኤሎችን በማምረት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ያላት ተሳትፎም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
“ፋታህ -1” የተባለው የሀይፐርሶኒክ ሚሳኤል በዚህ ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን ከድምጽ ፍጥነት በአምስት እጥፍ 6100 ኪሎሜትር በሰአት እንደሚምዘገዘግ ይነገርለታል፡፡
ከዚህ ባለፈ “ኢማድ 1” እና “ሲጂል” የተባሉ ከ1500 - 2500 ኪሜ ርቀት የሚጓዙ ሚሳኤሎችን በማምረት ላይ እንዳለች ወታደራዊ መረጃዎችን የሚያወጡ ተቋማት አመላክተዋል፡፡
ወታደራዊ ተንታኞች ኢራን እያመረተቻቸው የሚገኙ አዳዲስ ሚሳኤሎች እና በቀድሞዎቹ ላይ እያደረገች ያለቸው ማሻሻያ እስራኤል የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂዎቿን እንድትፈትሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡