ኢራን የታጠቀቻቸው የሚሳይል ጦር መሳሪያዎች እና የእስራኤል የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂ ምን ይመስላል?
በሺዎች የሚቆጠሩ የባላስቲክ እና ክሩዝ ሚሳኤል ባለቤት የሆነችው ኢራን በትላንት ምሽቱ ጥቃት 200 ሚሳይሎችን ጥቅም ላይ አውላለች
ወታደራዊ ተንታኞች የኢራን አዳዲስ ሚሳይሎች እስራኤልን የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂዎችን እንድትፈትሽ የሚያስገድዱ ናቸው ብለዋል
ኢራን የታጠቀቻቸው የሚሳይል ጦር መሳሪያዎች እና የእስራኤል የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂ ምን ይመስላል?
የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና የሚገኝበትን ወቅታዊ ከፍተኛ ውጥረት ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ሁነት ትላንት ምሽት ተፈጥሯል፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ለፈጸመችው ጥቃት በጋራ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ አስታወቁ
ኢራን በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የሚሳይል ጥቃት ማጠናቀቋን ገለጸች
የሀማስ እና የሄዝቦላ መሪ ግድያን ተከትሎ ቴሄራን ምሽቱን በቴልአቪቭ ባደረሰችው ጥቃት የክሩዝ እና የባላስቲክ ሚሳይሎችን ጥቅም ላይ አውላለች፡፡
ለመሆኑ የኢራን የሚሳኤል ጦር መሳርያዎች አቅም እና የእስራኤል የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂዎች ምን ይመስላሉ፡፡
የኢራን ሚሳኤሎች አቅም
ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ በ2023 ባወጣው ሪፖርት ቴሄራን የተለያየ ርቀት የሚሸፍኑ ከ 3 ሺህ በላይ ባላስቲክ ሚሳይሎች ባለቤት መሆኗን ጠቅሷል፡፡
እነዚህ ባላስቲክ ሚሳይሎች ከምድር ከባቢ አየር ውጭ በመውጣት ወደ ኢላማቸው በቀጥታ የመምዘግዘግ አቅም አላቸውም ነው የተባለው፡፡
ሲኤንኤን ወታደራዊ ተንታኞችን አነጋግሮ ባዘጋጀው ዘገባ በምሽቱ ጥቃት “ሻሀብ- 3” የተባለውን እስከ 2 ሺህ ኪሎሜትር የሚምዘገዘገውን ሚሳኤል ኢራን መጠቀሟን ጠቅሷል፡፡
ከ760 -1200 ኪሎግራም ድረስ የሚመዝን የጦር አረር የሚሸከመው ይህ ሚሳኤል በርቀት መቆጣጠርያ አልያም ከሚሳይል ማስወንጨፊያዎች መተኮስ የሚችል ነው፡፡
ሌላው የሀገሪቱ አዲስ ምርት የሆነው “ፋታህ -1” የተባለው የሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ሲሆን ከድምጽ ፍጥነት በአምስት እጥፍ 6100 ኪሎሜትር በሰአት መወንጨፍ ይችላል፡፡
ይህኛው ሚሳይል በምሽቱ ጥቃት ለመጀመርያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሳይውል እንዳልቀር ተገምቷል፡፡
ሀይፐር ሶኒክ በሚል የሚገለጹት ሚሳይሎች ከባላስቲክ የሚለያቸው የሚጓዙበት ፍጥነት ፣ የሚያካልሉት ርቀት እና በአየር ላይ ያላቸው የመተጣጠፍ አቅም በአየር መቃወሚያዎች ለመመታት አስቸጋሪ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡
ወታደራዊ ተንታኞች ኢራን እያመረተቻቸው የሚገኙ አዳዲስ ሚሳይሎች እና በቀድሞዎቹ ላይ እያደረገች ያለቸው ማሻሻያ እስራኤል የአየር መቀወሚያ ቴክኖሎጂዎቿን እንድትፈትሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የእስራል የአየር መቃወሚያዎች (ሚሳኤል ዲፌንስ ሲስተም)
እስራኤል በዋናነት ጥቅም ላይ የምታውላቸው ሶስት የሚሳኤል መከላከያ ቴክኖሎጂዎች ሲኖሯት አይርን ዶም ፣ “ዴቪድ ስሊንግ” እና “አሮው ስስተም” በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡
“አይረን ዱም” የምሽቱን የኢራን በአይነቱ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት በመመከት ደረጃ ያለው አቅም ዝቅተኛ ነው፡፡
ይህ የአየር መቃወሚያ ማክሸፍ የሚችለው እስከ 70 ኪሎሜትር ድረስ የሚተኮሱ የአጭር ርቀት ሚሳይሎችን ብቻ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በአንጻሩ “ዴቪድ ስሊንግ” ከ300 – 1000 ኪሜ የመካከለኛ ርቀት ሚሳይሎችን ማክሸፍ ሲችል “አሮው ሲስተም” የተባለው በትላንቱ ጥቃት በርካታ ሚሳይሎችን አውድሟል የተባለው መቃወሚያ ደግሞ እስከ 2400 ኪሜ ድረስ የሚጓዙ የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ለመቃወም አገልግሏል፡፡
በአሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት የተመረቱት “አሮው- 2” እና “አሮው -3” የአየር መቃወሚያዎች ሚሳይሎች የሀገሪቱን የአየር ክልል ጥሰው ከገቡበት ቅጽበት አንስተው ለማክሸፍ ተመራጭ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
ወደ ቀጠናዊ ጦርነት እየተንደረደረ በሚመስለው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡
ምሽቱን በአይነቱ ከፍተኛ የተባለውን የሚሳኤል ጥቃት ያስተናገደችው እስራኤል ኢራንን ጨምሮ በቀጠናው በሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ላይ የአጸፋ ጥቃት እንደምትፈጽም ዝታለች። ይህም የተፈራውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት እንዳያስነሳ በቀጠናው ከፍተኛ የስጋት ጥላን አጥልቷል፡፡