የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ የፕሬዝደንት ራይሲን ሞት ተከትሎ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን ማወጃቸውን አስታውቀዋል
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ የፕሬዝደንት ኢብራሂም ራይሲን ሞት ተከትሎ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን ማወጃቸውን አስታውቀዋል።
ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆሴን አሚር አብሎላሂያን ባለፈው እሁድ በተራራማው የሰሜን ምዕራብ ኢራን በደረሰው የሄሊኮፕተር መጋጨት አደጋ ህይወታቸው አልፏል።
አያቶላህ ለ"ውድ የኢራን ህዝብ" መጽናናትን እንደሚመኙ ተናግረዋል።
የ63 አመቱ ኢብራሂም ራይሲ ጠቅላይ መሪውን ካሚኒን ይተካሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር።
ቢቢሲ የኢራን የመንግስት ሚዲያዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው በፈረንጆቹ ሰኔ 28 አዲስ ፕሬዝደንት ለመተካት ምርጫ ይካሄዳል። ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሞሀመድ ሞክበር ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው ተሰይመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢራን ካቢኔ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን አሊ ባግሪ ካኒን ጊዜያዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርጓቸዋል።
የኢራን መንግስት ሚዲያዎች ራይሲን እና ሁሴን አብዶላሂያንን ጨምሮ አሳፍራ የነበረችው ሄሊኮፕተር አየሩ ጭጋጋማ በመሆኑ ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማረፋን መጀመሪያ ባወጡት ሪፖርት ገለጸው ነበር።
ሄሊኮፕተሩ አደጋ ያጋጠማት ራይሲ እና ፕሬዝደንት ኢልሃሞ አሊየቭ በተገናኙበት ለአዘርቤጃን ድንበር ቅርብ በሆነ ቦታ ነው።
እንደሚዲያዎቹ ከሆነ ራይሲ ወደ እዚያ አቅንተው የነበሩት ቂዝ ቋላሲ እና ኮዳፋሪን የተባሉ ሁለት ግድቦችን ለመመረቅ ነበር።
በትናንትናው እለት የኢራን ቀይ ጨረቃ የፕሬዝደንቱ እና በአደጋው የሞቱ የሌሎች ዲፕሎማቶችን አስከሬን መገኘቱን እና የፈለጋ ስራው መጠናቀቁን አረጋግጧል።
ለሀገሪቱ እስላሜዊ አብዮት ዘብ ቅርብ የሆነው የዜና አገልግሎት ታስኒም፣ እንደዘገበው ከሆነ የራይሲ የቀብር ስነ አስርአት በመጭው ማክሰኞ ይከወናል።
በወግ አጥባቂነት የሚያታወቁት ራይሲ በፈረንጆቹ 2021 የተካሄደውን ምርጫ በማሸነፍ ስምንተኛ ፕሬዝደንት መሆን ችለው ነበር።