በኢራን የተከሰከሰው አሜሪካ ሰራሹ ሄሊኮፕተር “ቤል 212” እውነታዎች
“ቤል 212” ሄሊኮፕተር በ1980ዎቹ መጀመሪያ ቴክስትሮን በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ መመረት ጀምሯል
አስቸጋሪ የአየር ጸባይን ተቋቁሞ የመብረር አቅም እንዳለው ሲነገርለት የቆየው ሄሊኮፕተር በኢራን ከተራራ ጋር ተጋጭቶ ተከስክሷል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው ሄሊኮፕተር በትላንትናው እለት መከስከሱ ይታወሳል።
ሄሊክፕተሩ አሜሪካ ሰራሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ መላምቶች ሲነሱ ቆይተዋል።
የኢራኑን ፕሬዝዳንት ጨምሮ 8 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው “ቤል 212” ሄሊኮፕተር መች እና የት ተመረተ?
“ቤል 212” የተሰኘው ሄሊኮፕተር መመረት የጀመረው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ቴክስትሮን በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ነው፡፡
የሄሊኮፕተሩ ዲዛይን ለተለያዩ አገልግሎቶች ምቹ መሆኑን ተከትሎ በአለም አቀፍ ገበያ ትርፋማ እና ተፈላጊ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ አስቸጋሪ የአየር ጸባዮችንም ተቋቁሞ የመብረር አቅም የተላበሰ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡
አብራሪዎችን ጨምሮ 13 ሰዎችን መያዝ የሚችለው ሄሊኮፕተር ባለፉት አመታት ለወታደራዊ፣ ለእሳት አደጋ መከላከል፣ ለግል መጓጓዣ እና ለነፍስ አድን ተልዕኮዎች ተመራጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በሰአት 260 ኪሎሜትር ሲጓዝ ድጋሚ ነዳጅ መሙላት ሳያስፈልገው በ20 ሺህ ጫማ (6100 ሜትር) ከፍታ ላይ 745 ኪሎሜትሮችን መጓዝ ይችላል፡፡
ከምቾት እና ከበረራ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የተጓዦቹን እና የአብራሪዎቹን ደህንንት የጠበቀ አሰራር እንዳለው ቢገለጽም አንዳንድ የአቪየሽን ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂዎቹ ቅርብ ግዜ ከተመረቱ ሄሊኮፕተሮች ጋር ሲነጻጸሩ ጊዜ ያለፈባቸው እና መሻሻል ወይም አብዴት መደረግ የማይችሉ ናቸው ተብሏል፡፡
ቤል 212 ሄሊኮፕተር የጥገና እና ሌሎች ወጪዎቹ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በጥቂት ሀገራት እና ግለሰቦች እጅ ይገኛል።፡
የታይላንድ ብሄራዊ ፖሊስ፣ የጃፓን የባህር ዘብ፣ የአሜሪካ የእሳት አደጋ መከላከል ተቋም እና የተለያዩ የህግ አስከባሪ ተቋማት፣ ሄሊኮፕተሩን በስፋት ከሚጠቀሙት መካከከል ይጠቀሳሉ፡፡
የኢራን አስተዳደር በአጠቃላይ ምን ያህል ቤል 212 ሄሊኮፕተር እንደሚጠቀም በግልጽ ባይታወቅም ፍላይት ግሎባል የተሰኝ ተቋም በቴህራን አየር እና ባህር ሀይል እጅ እሁድ እለት ፕሬዝዳንቷን ይዞ የተከሰከሰው አይነት 10 ተመሳሳይ ሞዴል ሄሊኮፕተሮች ይገኛሉ ብሏል፡፡
“ቤል 212” ለመጨረሻ ጊዜ የመከስከስ አደጋ ያጋጠመው በመስከረም 2023 በአረብ ኤሜሬትስ ሲሆን፥ ከኢራኑ ፕሬዝዳንት አደጋ ጋር የሚመሳሰል አደጋ በ2018 ተከስቶ የ4 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ሬውተርስ አስታውሷል።