የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ህልፈት ተከትሎ የዓለም ሀገራት መሪዎች ምን አሉ?
ፕሬዝዳንት ብራሂም ራይሲና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያንም በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው አልፏል
በርካታ የዓለም አሀገራት ሀዘናቸውንና አጋርነታቸውን ሲገልጹ አሜሪካ እስካሁን ዝምታን መርጣለች
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በርካታ የዓለም ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸውነና አጋርነታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያንም ጨምሮ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣንት በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው አልፏል።
ይህንን ተከትሎም የተለያዩ የዓለም ሀገራት ሀዘናቸው በመግለጽ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አሜሪካ እስካሁን ዝምታን መምረጧ አነጋጋሪ ሆኗል።
የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያን በፕሬዝዳንት ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በራሳቸው እና በአረብ ኢምሬትስ ህዝብ ለኢራናውያን አስተላልፈዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት ሀገራቸው አረብ ኢምሬት ከኢራን ጎን መሆኗን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የፕሬዝዳንት ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያን ህይወት በቀጠፈው የሄሊኮፕተር አደጋ ማዘናቸውን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ህዝብ፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና በራሳቸው ስም ለኢራናውያን መጽናናትን ተመኝቷል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንም በፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ድንገተኛ ህልፈት ማዘናቸውን ገልጸው፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢራን ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፤ የፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ድንገተኛ ህልፈት አስደንጋጭና አሳዛኝ ሲሉ የገለጹ ሲሆን፤ በዚህ የሀዘን ወቅት ከኢራን ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የፕሬዝዳንት ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያን ህይወት በቀጠፈው አስደንጋጭ አደጋ ማዘናቸውን ገልጸው፤ ለኢራናውያን መጽናናትን ተመኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አከለውም፤ “ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ሙሉ ህይወቱ እናት ሀገራሩን ለማገልገል የሰጠ ድንቅ ፖለቲከኛ ነበር” ብለዋል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸባዝ ሻሪፍ፤ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ማጣት በጣም አሳዛኝ ነው ያሉ ሲሆን፤ ሀገራቸው ፓኪስታን ፕሬዝዳንት ራይሲን ለማሰብ የአንድ ቀን ብሄራዊ የሀዘን ቀን ማወጇ አስታውቀዋል።
የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ፤ በፕሬዝዳንት ራይሲ ህልፈት መደንገጣቸውን ገልጸው፤ ፕሬዝዳንት ራይሲ የቅርበ ወዳጅ እና ልዩ መሪ ነበር ሲሉ አሞካሽተዋል።
የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሼል፤ የፕሬዝዳንት ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚራብዶላሂያን ህልፈት ተከትሎ ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ለቤተሰቢቻቸው እና ለኢራናውያን መጽናናትን ተመኝተዋል።
የየመኑ ሃውቲ መሪ ሞሃመድ አሊ አልሃውቲ፤ ለፕሬዝዳንት ራኢሲ እና ሌሎችም ለተሰው ኢራናውያን አመራች ቤተሰቦች እና ኢራናውያን ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ጋዛን የሚያስተዳድረው እና ከእስራኤል ጋር ውጊያ ላይ የሚገኘው ሃማስም፤ በፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ህልፈት ሀዘኑን መግለጹ ተነግሯል።