አል ናስር ከ10 ቀናት በፊት የኢራኑን ፐርሴፖሊስ ለመግጠም ወደ ቴህራን አቅንቶ እንደነበር ይታወሳል
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኢራኑ ኤስፒናስ ፓላስ ሆቴል ሃውልት ቆሞለታል።
በቴህራን የሚገኘው ሆቴል ሮናልዶ እና የአል ናስር ክለብ አጋሮቹ ከ10 ቀናት በፊት ያረፉበት ሆቴል ነበር።
አል ናስር በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ የኢራኑን ፐርሴፖሊስ ለመግጠም ባቀናበት ወቅት ክርስቲያኖ ሮናልዶ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት የሚታወስ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሮናልዶ ደጋፊዎች አደባባይ በመውጣት አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን፥ እስካረፉበት ኤስፒናስ ፓላስ ሆቴል በመሸኘትም ፍቅራቸውን ገልጸውለታል።
ተጫዋቹ ኢራናዊያን ታዳጊዎችን ለማበረታታት እና ከህልማቸው ጋር ለማገናኘት ሲጥርም ታይቷል።
ሮናልዶ ቴህራን ከገባ አንስቶ እስኪመለስ የኢራን እና አለማቀፉን መገናኝ ብዙሃን ትኩረት የሳበ ሲሆን፥ በትናንትናው እለት ደግሞ በቴህራን ለ36 ስአታት ቆይታ ያደረገበት ሆቴል ሮናልዶን ዜና የሚያደርግ መረጃን አጋርቷል።
ኤስፒናስ ፓላስ ሆቴል የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊውን ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሃውልት በሰገነቱ ላይ በክብር ማስቀመጡን አስታውቋል።