ሮናልዶ በሶሪያና ቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ሲከሰቱም ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል
ፖርቹጋላዊው የእግርኳስ ፈርጥ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሞሮኮ ርዕደ መሬት ቤታቸው ለፈረሰባቸው ዜጎች አለሁላችሁ ብሏል።
ሮናልዶ በማራካሽ ከተማ የገነባው ባለአራት ኮከብ ሆቴል ተጎጂዎች እንዲጠለሉበት መፍቀዱን ማርካ ጋዜጣ ዘግቧል።
“ፔስታና ሲአር7 ማራካሽ” 174 የመኝታ ክፍሎችን የያዘና 53 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ ሆቴል ነው ተብሏል።
አርብ አመሻሽ ላይ የተከሰተውና በሬክተር ስኬል ሲለካ 6 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ማራካሽ እና አካባቢውን አፈራርሷል።
በአደጋው ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ ከ1 ሺህ 400 በላይ ሰዎችም መቁሰላቸው ተነግሯል።
የመንግስት እና የግል ተቋማትም በፍጥነት ወደ ጊዜያዊ መጠለያነት እየተለወጡ ይገኛሉ።
ያም ሆኖ ቤቶችን ወደ ፍርስራሽነት የለወጠው አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ባለፉት ሁለት ቀናት በፈራረሱ ቤቶቻቸው ጥግ ሸራ ዘርግተው እንዲተኙ አስገድዷል።
በርዕደ መሬት አደጋው የተጎዱትን ለመደገፍ የተጀመረው ጥረትም ቀጥሏል።
የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ለመድረስ ደም የለገሱ ሲሆን፥ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አሽራፍ ሃኪሚ ለወገኖቻችን በፍጥነት እንድረስ የሚል ጥሪውን አቅርቧል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶም በኳታሩ የአለም ዋንጫ ሀገሩን ከውድድር ያስወጣችውን ሞሮኮ ለመደገፍ ሆቴሉን ለተጎጂዎች ክፍት አድርጓል።
ሮናልዶ በዚሁ የፈረንጆቹ አመት የካቲት ወር ላይ በሶሪያ እና ቱርክ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን የቀጠፈ የርዕደ መሬት አደጋ ሲደርስ ድጋፍ መላኩ ይታወሳል።
የሳኡዲው አል ናስር ክለብ ተጫዋቹ በሁለት አውሮፕላኖች የነፍስ አድን ምግብ እና አልባሳትን በመላክ ሰብአዊነቱን ማሳየቱ አይዘነጋም።
በኔፓል በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሲያጋጥምም ሆነ በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ወረርሽኝ ሲከሰት ሮናልዶ ድጋፉን አሳይቷል።
ተጫዋቹ እንደ “ዩኒሴፍ” እና “ሴፍ ዘ ቺልድረን” ካሉ ተቋማት ጋር በመተባበር በመላው አለም ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብና በማገዝም ይታወቃል።