ኢራን ከነዳጅ ንግድ 26 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገለጸች
ሀገሪቱ እስከ ቀጣዩ መጋቢት ድረስ ከወጪ ንግድ 116 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች
በነዳጅ ሀብቷ ከዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ኢራን በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት ነዳጅ ለዓለም ገበያ ማቅረብ አልቻለችም
ኢራን ከነዳጅ ንግድ 26 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገለጸች፡፡
በነዳጅ ሀብቷ ከዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ኢራን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ውጪ ሀገራት ከላከችው ነዳጅ 26 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ ነዳጅ ሚኒስትር ጃቫድ አውጂ እንዳሉት የኢራን ወጪ ንግድ ገቢ የሰባት በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ሀገሪቱ እስከ መጭው መጋቢት ወር ድረስ ከወጪ ንግድ 116 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች፡፡
ኢራን ከአሜሪካ ጋር ባላት የዲፕሎማሲ መሻከር ምክንያት ማዕቀብ የተጣለባት ሲሆን ይህም ነዳጅን ጨምሮ ምርቶቿን ለዓለም ገበያ በቀላሉ ማቅረብ አልቻለችም፡፡
ቻይና እና ሌሎች የእስያ ሀገራት ዋነኛ የንግድ አጋሯ ሲሆኑ ነዳጇን ከዓለም ገበያ ዝቅ ባለ ዋጋ ለመሸጥ እንደተገደደችም ተገልጿል፡፡
ኢራን ግዙፍ የጦር መርከቧን ወደ ቀይ ባህር መላኳ ተነገረ
ዓለም አቀፉ የነዳጅ ላኪ ሀገራት ባወጣው መረጃ መሰረት ቬንዙዌላ ባላት ነዳጅ ሀብት የዓለማችን ቀዳሚ የነዳጅ ሀብታም ሀገር ስትሆን ሳውዲ አረቢያ እና ካናዳ ደግሞ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሀገራት ናቸው፡፡
ኢራን፣ ኢራቅ እና ኩዌት ደግሞ በቅደም ተከተላቸው መሰረት ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በነዳጅ ሀብቷ 10 ደረጃ ላይ የምትገኘው አሜሪካ ከ2018 ጀምሮ የዓለማችን ቀዳሚዋ ነዳጅ አምራች ሀገር ስትሆን በ2022 ላይ ብቻ በየቀኑ በአማካኝ 18 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ አምርታ ለገበያ አቅርባለች፡፡
ሳውዲ አረቢያ በ2022 ዓመት ብቻ 311 ቢሊዮን ዶላር ከነዳጅ ሽያጭ ገቢ ማግኘቷ ተገልጿል፡፡