“ጀግኖቹ የፍልስጤም ታጣቂዎች ጽዮናዊውን መንግስት በአጭር ጊዜ ይደመስሱታል” - ኢራን
ቴህራን “በእስራኤል” የተገደሉት ጄነራሏ ቀብር ሲፈጸም ፈጣን የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች
እስራኤል የኢራን ጀነራልን በሶሪያ ገድላለች ለሚለው ወቀሳ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም
ኢራን ለ33 አመታት ያገለገሏትንና “እስራኤል በሶሪያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የተገደሉትን” ጀነራሏን በዛሬው እለት በክብር ሸኝታለች።
የሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒንን ጨምሮ በርካታ ኢራናውያን በሳይድ ራዚ ሙሳቪ አስከሬን ሽኝት ስነስርአት ላይ ተገኝተዋል።
ሃሚኒ በሃዘን መግለጫቸው “ሰማዕቱ ሙሳቪ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሀገሩን አገልግሏል” ብለዋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዡ ሜጀር ጄኔራል ሆሴን ሳላሚም የነጻነት ትግሎችን በማደራጀትና በመምራት ልዩ ብቃት የነበራቸውን ሳይድ ራዚ ሙሳቪ ግድያ በቀላሉ እንደማያዩት ነው የተናገሩት።
“የምንወስደው የበቀል እርምጃ የጺዮናዊውን መንግስት ከማስወገድ ያነሰ አይሆንም” ሲሉም ዝተዋል።
“ጀግኖች እና የተከበሩ” ሲሉ ያሞካሿቸው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖችም በአጭር ጊዜ የእስራኤልን መንግስት እንደሚደመስሱት ገልጸዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በጀነራል ሙሳቪ አስከሬን ሽኝት ላይ የተገኙ ኢራናውያን “ሞት ለአሜሪካ፤ ሞት ለእስራኤል” የሚል መፈክር ሲያሰሙ ነበር ተብሏል።
እስራኤል ግን እስካሁን ከሙሳቪ ግድያ ጀርባ ስለመኖሯ ምንም ማረጋገጫ አልሰጠችም፤ ማስተባበልም አልፈለገችም።
አይሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ስለሙሳቪ ግድያ ተጠይቀው በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ “የእስራኤልን ብሄራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የትኛውንም እርምጃ እንወስዳለን” ማለታቸውም በቴህራን እንደማረጋገጫ ተወስዷል።
እስራኤል ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ በጋዛ ጦርነት ስታውጅ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ ይገኛሉ፤ በኢራቅና ሶሪያ የሚገኙ ታጣቂዎችም በአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።
እስራኤልም በሶሪያ ቴህራን ትደግፋቸዋለች ባለቻቸው ታጣቂዎች ላይ ለአመታት ተከታታይ ጥቃት መውሰዷ ይታወሳል።
የበሽር አል አሳድ መንግስትን ጦር ለማማከር ሶሪያ የነበሩት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አማካሪ ሳይድ ራዚ ሙሳቪን ከስራ ወደ ቤታቸው ሲያመሩ በአየር ጥቃት ገድላቸዋለች ብላለች ኢራን።
ቴህራን በቀጥታ ወይም በምደግፋቸው ታጣቂዎች የሙሳቪን ግድያ ካልተበቀልኩ አልተኛም ብላለች።
የመካከለኛው ምስራቅ ባላንጣዎች አዲስ ፍጥጫ በጋዛው ጦርነት የእጅ አዙር ተፋላሚዎችን እየጨመረ ጦርነቱን ለወራት ሊያራዝመው እንደሚችል ተገምቷል።