ኢራን ግዙፍ የጦር መርከቧን ወደ ቀይ ባህር መላኳ ተነገረ
“አልቦርዝ” የተሰኘችው የጦር መርከብ በባብ አልማንደብ አቋርጣ ቀይ ባህር መግባቷን የቴህራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል
አሜሪካ እና ብሪታንያ የኢራን የጦር መርከብ ቀይ ባህር ስለመግባቷ ማረጋገጫ አልሰጡም
ኢራን “አልቦርዝ” የተሰኘችውን የጦር መርከቧን ወደ ቀይ ባህር መላኳ ተነገረ።
መርከቧ በባብ አል ማንደብ በኩል ወደ ቀይ ባህር መዝለቋን ታስኒም የተባለው የኢራን የዜና ወኪልን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
የአልቦርዝ ተልዕኮ ምን እንደሆነ በዝርዝር ያልጠቀሰው ታስኒም መርከቧ መቼ ቀይ ባህር እንደገባችም አላብራራም።
ቴህራን ማረጋገጫ ባትሰጥበትም “አልቦርዝ” የተሰኘችው መርከብ ቅዳሜ እለት ቀይ ባህር መግባቷ ተነግሯል።
የኢራን መከላከያ ሚኒስትር ሞሀመድ ሬዛ አሽቲያኒ ከሁለት ሳምንት በፊት ቴህራን የበላይነት በያዘችበት የቀይ ባህር ቀጠና ማንም እንዲፈነጭበት አንፈቅድም የሚል አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።
ቴህራን ግዙፍ የጦር መርከቧን ወደ ቀይ ባህር ማስገባቷ የተገለጸው አሜሪካ ሶስት የሃውቲ ታጣቂዎች ጀልባዎችን መትታ ማስመጧና ሁሉንም ታጣቂዎች መግደሏን ባሳወቀች ማግስት ነው።
የኢራን የደህንነት ሹም አል አክባር አህመዲን ከሃውቲ ቡድን ዋነኛ ተደራዳሪ መሀመድ አብዱልሰላም ጋር ሲመክሩ ሃውቲዎች ለፍልስጤማውያን ያሳዩትን ድጋፍ ማድነቃቸውን ኢርና የተባለው የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
በመሆኑም የ”አልቦርዝ” ቀይ ባህር መግባት ሃውቲዎች በአሜሪካ እና በምትመራው የሀገራት የጋራ የባህር ቅኝት ግብረሃይል ሊደርስባቸው የሚችለውን ጥቃት ለመመከትና የአጻፋ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
በቀይ ባህር አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቧን ያሰማራችው አሜሪካም ስለኢራን መርከብ እንቅስቃሴ አስተያየት መስጠት አልፈልግም ብላለች።
ብሪታንያም የየመኑን ታጣቂ ቡድን የምታግዘው ኢራን በቀይ ባህር ውጥረት ከማባባስ እንድትታቀብ መጠየቋን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኢራን ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በአካባቢው የንግድ መርከቦች ደህንነትን ለማረጋገጥና የባህር ላይ ዝርፊዎያዎችን ለመከላከል የጦር መርከቦቿን ስታሰማራ እንደነበር ተገልጿል።
የአሁኑ የጦር መርከብ ስምሪቷ አላማ በግልጽ ባይነገርም አሜሪካ ያደራጀችው የባህር ቅኝት ግብረሃይል በሃውቲ ታጣቂዎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት መመከት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።