የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ለፍልስጤማውያን ድል ለእስራኤል ሽንፈት ነው - ሃሚኒ
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው ስምምነቱ በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ስላም ለማስፈን በር ከፋች ነው ብለዋል
የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማጽደቅ የሚያደርገው ስብሰባ እየተጠበቀ ነው
እስራኤል እና ሃማስ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ለፍልስጤማውያን ትልቅ ድል ነው አለች ኢራን።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "የጋዛ ህዝብ ትዕግስት እና የፍልስጤማውያን ብርቱ ትግል እስራኤል እንድታፈገፍግ አድርጓል" ብለዋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብም "የተኩስ አቁም ስምምነቱ እና የጦርነቱ መቆም ለፍልስጤማያን ትልቅ ድል ለእስራኤል ደግሞ መራራ ሽንፈት ነው" የሚል መግለጫን አውጥቷል።
ቴህራን ድጋፍ የምታደርግለውት የየመኑ ሃውቲም በተኩስ አቁም ስምምነቱ ዙሪያ የደስታ መልዕክታቸውን ካስተላለፉት መካከል ይገኝበታል።
የሃውቲዎች ቃልአቀባይ ያህያ ሳሬ "ፍልስጤማውያን በእስራኤል በምታደርሰውን ከባድ ጭቆና በመቃወም ታሪካዊ ጽናት አሳይተዋል" ማለታቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በሶስት ምዕራፍ ይተገበራል በተባለው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ስምምነቱ በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ስላም ለማስፈን በር ከፋች ነው ብለዋል።
እስራኤል በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት የተመሰረተባትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የምትመራው ደቡብ አፍሪካ መንግስትም የ15 ወራቱን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰውን ስምምነት አድንቋል።
የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ በአሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ አደራዳሪነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማጽደቅ በዛሬው እለት የሚያካሂደው ስብሰባ እየተጠበቀ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት "ሃማስ ባለቀ ስአት ስምምነቱ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲካተቱ እየጠየቀ ነው" በሚል ስብሰባው መራዘሙን ይፋ ማድረጉን ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል ተደራዳሪዎች ከዶሃ እንደተመለሱ ስብሰባው እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፥ ስምምነቱ ከጸደቀ ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።