እስራኤል እና ሀማስ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ተገለጸ
ስምምነቱ የመካከለኛው ምስራቅን ያመሰቃቀለው 15 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት እንዲቆም በር የሚከፍት ነው ተብሏል
ስምምነቱ የተደረሰው እስራኤል የሀማስ እና የሂዝቦላ ከፍተኛ መሪዎችን ከገደለች በኋላ ነው
እስራኤል እና ሀማስ 15 ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት የሚያስቅም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተዘግቧል።
ሁለቱ ተፋላሚዎች በጋዛ እያካሄዱ ያሉትን ጦርነት ለማቆም እና የእስራኤል ታጋቾችን በፍልስጤማውያን እስረኞች ለመለዋወጥ በዛሬው እለት መስማማታቸውን ሮይተርስ በድርድሩ ዙሪያ መረጃ የደረሳቸውን ባለስልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።
ስምምነቱ የመካከለኛው ምስራቅን ያመሰቃቀለው 15 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት እንዲቆም በር የሚከፍት ነው ተብሏል።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኃይት ሀውስ ሊገቡ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው የተደረሰው ስምምነት፣ ግብጽ እና ኳታር በአሜሪካ እየተደገፉ ለበርካታ ወራት የማደራደር ጥረት ማድረጋቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።
የእስራኤል ወታሮች በጋዛ ላይ ወረራ የፈጸሙት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ከሁለት አመት በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት 1200 ሰዎችን ከገደለ እና ሌሎች 250 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር። እስራኤል በፈጸመችው መጠነሰፊ የአየር እና እግረኛ ጦር ጥቃት እስካሁን ከ 46 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገዳላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የጋዛ ነዋሪዎች የእስራኤልን ጥቃት ለመሸሽ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
በዓለ ሲመታቸው እየተቃረበ ያሉት ትራምፕ በቶሎ ስምምነት እንዲደረስ እንደሚፈልጉና ታጋቾች የማይለቀቁ ከሆነ ከባድ ቅጣት እንደሚያደርሱ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። የተጋቾቹ መለቀቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁና በቀኝ ዘመም መንግስታቸው ላይ የተነሳውን የህዝብ ቁጣ እንደሚያቀዘቅዘው ተገልጿል። ግጭቱ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ወደሚገኙበት ሊባኖስ፣ ኢራቅ እና የመን ተስፋፍቷል።
ስምምነቱ የተደረሰው እስራኤል የሀማስ እና የሂዝቦላ ከፍተኛ መሪዎችን ከገደለች በኋላ ነው።