የሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ አስከሬን ሽኝት በቴህራን እየተካሄደ ነው
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒም በቴህራን ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን የጸሎት ስነስርአት መርተዋል
የሃኒየህ ስርአተ ቀብር በነገው እለት በኳታር ይካሄዳል
የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ አስከሬን ሽኝት በቴህራን እየተካሄደ ነው።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በቴህራን ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን የጸሎት ስነስርአት ሲመሩ አዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ከጎናቸው ታይተዋል።
የሃኒየህ እና ጠባቂያቸው አስከሬን በተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ በአዛዲ አደባባይ ሲንቀሳቀስም ኢራናውያን በነቂስ በመውጣት አበባዎችን በመበተን ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
የሃማሱ መሪ የአስከሬን ሽኝት እንደተጠናቀቀም ወደ ኳታር ተወስዶ ስርአተ ቀብሩ በነገው እለት እንደሚፈጸም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የእስራኤልን ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ያመለጡት ሃኒየህ ለአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ወደ ቴህራን ባቀኑበት ህይወታቸው አልፏል።
እስራኤል እስካሁን ለግድያው ሃላፊነቱን እንደማትወስድ ብትገልጽም ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ ሁሉንም የሃማስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች እንደምትገድል መዛቷ ይታወሳል።
የኢራን ባለስልጣናት የሃኒየህን ግድያ እየመረመሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን እስካሁን ዝርዝር የምርመራ ውጤቱ ይፋ አልሆነም።
የሶስት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን ያወጀችው ቴህራን በግዛቷ ለተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ በማድረግ አጻፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጻለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ “ኢራን የሃኒየህን ደም ትበቀላለች” ያሉ ሲሆን፥ ቴህራን ከወራት በፊት እንደፈጸመችው አይነት የሚሳኤል ጥቃት ትፈጽማለች ተብሎ ይጠበቃል።
እስራኤልም ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን የሚያከሽፉ የአየር መቃወሚያ ስርአቶቿን በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ማዘዟ ነው የተዘገበው።
በሊባኖስ መዲና ቤሩት ከፍተኛ የሄዝቦላህ አዛዥን ከገደለች በኋላ በኢራን የሃማስ መሪን መግደሏ ሊባኖስ እና ኢራንን ለጦርነት የመጋበዝ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛው ጦርነት ቢቆም ስልጣናቸው ማክተሙና በጦር ወንጀል መጠየቃቸው አይቀሬ ነው የሚሉ ተንታኞችም የሃኒየህ ግድያ ቀጠናዊ ጦርነት በመክፈት አሜሪካን ስቦ የማስገባት እቅዳቸው አካል መሆኑን ያነሳሉ።
እስራኤል በሶሪያ የሚገኘውን የኢራን ኤምባሲ መምታቷን ተከትሎ ቴህራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችና ድሮኖችን ወደ እስራኤል መተኮሷ ይታወሳል።
የሃማስ መሪ በቴህራን መገደልም ሉአላዊነቷን የተዳፈረ መሆኑን በማመን ከበድ ያለ የአጻፋ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልና በሊባኖስ፣ የመን፣ ሶሪያ እና ኢራቅ የምትደግፋቸው ቡድኖችም የተቀናጀ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚለው ስጋት አይሏል።
የሃኒየህ ግድያ የጋዛ የተኩስ አቁም ድርድሮችን እና ከ100 በላይ ታጋቾችን የማስለቀቅ ሂደት አሰናክሎ የፍልስጤማውያንንም ሆነ የታጋቾቹን ሰቆቃ አስቀጥሏል።