ኢራን የሃማሱን የፖለቲካ መሪ ግድያ እንደምትበቀል ዛተች
የሀገሪቱ ሀይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ሀሚኒ በድንበራችን ውሰጥ ለተከሰተው ወንጀል ተገቢውን ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል
ግድያውን ተከትሎ ኢራን እና ሃመስ እስራኤልን ተጠያቂ ቢያደርጉም ሀገሪቱ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም አላለችም
ኢራን የሃማሱን የፖለቲካ መሪ ግድያ እንደምትበቀል ዛተች
የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ በኢራን መዲና ቴህራን በተፈጸመባቸው የሚሳኤል ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል፡፡
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል በሚደረጉ ድርድሮች ዋነኛ ሰው ሆነው የዘለቁት እስማኤል ሀኒየህ በዛሬው እለት በተሄራን መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን እና ሀማስን ጨምሮ ሙስሊም ሀገራት እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀን በቤሩት የሂዝቦላ ከፍተኛ ወታደራዊ ሃላፊን መግደሏን ያስታወቀችው እስራኤል በሃማሱ ዋና ሰው ሀኒየህ ግድያ ዙርያ እስካሁን ምንም አላለችም፡፡
የኢራን ሀይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ሀሚኒ በድንበር ክልላችን ውስጥ ለተከሰተው ወንጀል በእጥፍ አባዝተን ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ሃሚኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ በሰፈረው ጽሁፍ “ወንጀለኛው ጺዮናዊ አገዛዝ በቤታችን የሚገኝ እንግዳ ላይ ጥቃት በመሰንዘር አሳዝኗናል፤ በተመሳሳይ ሰአት ደግሞ በራሱ ላይ መሸከም የማይችለው ከባድ ቅጣትን አዟል”ብለዋል።
በተመሳሳይ አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዤሽኪን “እስራኤል ለፈሪ ድርጊቷ ዋጋዋን ታገኛለች” ሲሉ ዝተዋል፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ በበኩሉ “የዛሬው ጥቃት እስራኤል ለአለም አቀፍ ህጎች የማትገዛ የወንጀለኞች ስብስብ መሆኗን የሚያመላክት ነው ቴልአቪቭ ለከፍተኛ ቅጣት እራሷን ታዘጋጅ” ብሏል፡፡
እስማኤል ሀኒየህ ምንም እንኳን በጋዛ ሆነው ጦርነቱን በቀጥታ አይምሩ እንጂ ለሀማስ ፖለቲካዊ ድጋፎችን እና የዲፕሎማሲ ስራዎች በመስራት ዋነኛ ሰው ናቸው፡፡
ሀኒየህ ሀማስ እና እስራኤልን ለማደራደር በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ከአደራዳሪ እና ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመገናኝት የቡድኑን አቋም ወክለው በመነጋገር ይታወቃሉ፡፡
የፖለቲካ ሃላፊው ሞት በሀማስ እና በእስራኤል መካከል ለማድረግ የታሰበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችል የተለያዩ ተንታኞች ሀሳባቸውን እያጋሩ ነው፡፡
የሀማስን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቅም ሳላወድም የጋዛውን ጦርነት አላቆምም በሚል አቋሟ የጸናችው እስራኤል የቡድኑን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ኢላማ በማድረግ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
ከወራት በፊትም የሐማስ ምክትል የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ ሳሌህ አል አሩሪን በሊባኖስ መግደሏ ይታወሳል፡፡
ሀኒየህ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የታዩት በቴሄራን በተካሄደው የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ሲሆን በቀጣይ በሚደረጉ ስራዎች ዙሪያ ለመምከር በሚል በቴሄራን እንደቆዩም በመግለጫው ለይ ተጠቅሷል፡፡
እስማኤል ሀኒየህ በፈረንጆቹ 2021 ላይ በተካሄደ ምርጫ የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ተደርገው የተመረጡ ሲሆን እስከ 2025 ድረስ በሀላፊነት እንደሚቆዩ ይጠበቅ ነበር፡፡