እስራኤል ቤሩት ውስጥ ከፍተኛ የሂዝቦላ አዛዥን ገደልኩ አለች
እስራኤል የሊባኖሱን ሄዝቦላ ተጠያቂ ባደረገችበት ከሶስት ቀናት በፊት በተፈጸመው ጥቃት 12 ተማሪዎች ተገድለዋል
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት በአየር ጥቃት "የበርካታ እስራኤላውያንን ደም በእጁ ያለበት" ፉአድ ሹክር ተገድሏል ብለዋል
እስራኤል ቤሩት ውስጥ ከፍተኛ የሂዝቦላ አዛዥን ገደልኩ አለች
የእስራኤል ጦር፣ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለው ጎላን ሀይት ውስጥ የተፈጸመውን የተማሪዎች ግድያ ለመበቀል በወሰደው የበቀል እርምጃ የሄዝቦላን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በትናንትናው አለት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ውስጥ በአየር ጥቃት መግደሉን ገልጿል።
እስራኤል የሊባኖሱን ሄዝቦላ ተጠያቂ ባደረገችበት ከሶስት ቀናት በፊት በተፈጸመው ጥቃት 12 ተማሪዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት በአየር ጥቃት "የበርካታ እስራኤላውያንን ደም በእጁ ያለበት" ፉአድ ሹክር ተገድሏል ብለዋል።
"በዛሬው ምሽት የህዝባችን ደም ዋጋ እንደሚያስከፍል እና ኃይላችን የማይደርስበት ቦታ እንደማይኖር አሳይተናል" ሲሉ ሚኒስተሩ አክለው ተናግረዋል። ሄዝቦላ በዚህ ጉዳይ ወዳያውኑ መልስ አልሰጠም።
ሄዝቦላ ጎላን ሀይት ውስጥ በማጅዳል ሻምስ በዱሬዝ መንደር ውስጥ በሚገኝ የእግርኳስ ሜዳ ላይ በተፈጸመው እና የ12 ተማሪዎችን ህይወት በቀጠፈው የሮኬት ጥቃት እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል።
በቀጣናው ካሉ ሀገራት ውስጥ የአንዷ ከፍተኛ የጸጥታ ምንጭ ሹክር በጥቃቱ ቆስሎ መሞቱን እንዳረጋገጡለት ሮይተረስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር የሄዝቦላ ዋና ጸኃፊ ሀሰን ነስረላህ ዋና ረዳት፣ የጦርነት ዘመቻ አማካሪ እና የቅዳሜውን ጥቃት የመራ ነው ብሏል።
እስራኤል በቤሩት ከተማ ደቡባዊ ዳርቻ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሁለት ህጻናትን ጨምሮ ሶሰት ንጹሀን ሰዎች መገደላቸውን ዘገባው የአይን እማኖቸን ጠቅሶ ዘግቧል።
እስራኤል በቤሩት ላይ የፈጸመችው ጥቃት የሊባኖስ ባለስልጣናት እና የጋዛውን ሀማስ እና የየመኑን ሀውቲ ጨምሮ የሄዝቦላ የቀጣናው አጋሮች ተወግዟል።
የቤሩቱ ጥቃት ከተሰማ በኋላ የሀማስ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ኢራን ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን ሀማስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሀኒየህ የተገደሉት በኢራኑ ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያኒ በዓለ ሲመት ላይ ከተሳተፉ በኋላ ነው ብሏል ቡድኑ።