ኢራን የእስራኤልን የረቀቀ ሴራ ማክሸፏን አስታወቀች
እስራኤል ኢራን የጅምላ ጨራሽ ኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል
የእስራኤል የስለላ ኔትወርክ ዓለም አቀፍ ግብዓት አቅራቢ የንግድ ድርጅት መስሎ የኢራንን ኑክሌር ቴክኖሎጂ የማጋየት እቅድ ነበረው ተብሏል
ኢራን የእስራኤልን የረቀቀ ሴራ ማክሸፏን አስታወቀች፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ሚሳኤል ቴክኖሎጂን ለማውደም ያደረጉት ሴራ መክሸፉ ተገልጿል፡፡
ድርጊቱ ኢራን በታሪኳ ከተሞከረባት ሴራዎች ሁሉ ትልቁ የሚባል ነው የተባለ ሲሆን የእስራኤሌ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ለኢራኑ የኑክሌር ፕሮግራም ግብዓት አቅራቢ የንግድ ተቋም መስሎ ተገኝቷል ተብሏል፡፡
ኢራን ለኑክሌር ፕሮግራሟ የድሮን እና ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ልማት የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ማቀጣጠያ ግብዓት አቅራቢ ኩባንያ ስትፈልግ ሞሳድ የንግድ ድርጅት መስሎ ግብዓቱን ለማቅረብ እንደሞከሩ ተገልጿል፡፡
ኢራን ይህን የሞሳድ ውስብስብ ሴራ ባትደርስበት ኖሮ የባሊስቲክ ሚሳኤል እና አጠቃላይ የኑክሌር ቴክኖሎጂ ስራዋ በራሱ ጊዜ ፍንዳታዎችን በማስተናገድ ይወድም ነበር ተብሏል፡፡
የኢራን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር መህዲ ፋራሂ ለሀገሪቱ ዜና አገልግሎት እንዳሉት የሞሳድ ድርጊት የኢራንን ኑክሌር ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ የሚያጠፋ ነበር ብለዋል፡፡
ኢራን ንብረታቸውን ለውሻ ያወረሱ ጥንዶችን አሰረች
በፈረንጆቹ ግንቦት 2022 ላይ በምስራቃዊ ቴህራን ባለ የወታደራዊ ጦር መሳሪያዎች ልማት ማዕከል ላይ በደረሰ ፍንዳታ አንድ መሀንዲስን ሲገድል ሌላኛውን ማቁሰሉ ተገልጿል፡፡
ከእስራኤል በተጨማሪ በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ጊዜ የኢራንን የኑክሌር ቴክኖሎጂ ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር ኒዮርክ ታይምስ በወቅቱ ዘግቦ ነበር፡፡
ሮይተርስ ኢራን ባቀረበችው ሪፖርት ዙሪያ የእስራኤል መንግስትን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት አስታውቋል፡፡
ይሁንና ኢራን ከወራት በፊት ባሊስቲክ ሚሳኤል መታጠቋን ለዓለም ያበሰረች ሲሆን ለተለያዩ ሀገራትም የተለያዩ ዘመናዊ ድሮኖችን በመሸጥ ላይ እንደምትገኝም ተገልጿል፡፡