ድርጊቱ የሰው ልጆችን ሞራል ይጎዳል በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል
ኢራን ንብረታቸውን ለውሻ ያወረሱ ጥንዶችን አሰረች፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ኢራን ከሰሞኑ ጥንዶች ንብረቶቻቸውን ለውሻቸው ሲያወርሱ የተፈራረሙት ስምምነትንን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡
ይህን ተከትሎ በርካታ ኢራናዊያን በድርጊቱ ተገርመው አስተያየት የሰጡ ሲሆን አንዳንዶቹ እንዴት ይህን ሁሉ ንብረት ለውሻ ያወርሳሉ ለምን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አይሰጡም እና የመሳሰሉትን አስተያየቶች ተንጸባርቀዋል፡፡
ልጅ እንደሌላቸው የተገለጸው እነዚህ ጥንዶች መኖሪያ ቤትን ጨምሮ በርካታ ንብረቶቻቸውን ለውሻቸው ማውረሳቸው ተገልጿል፡፡
ጥንዶቹ ያላቸውን ንብረት ለውሻቸው እንዲያወርሱ ስምምነቱን ያስፈረመው የንግድ ድርጅት ሀላፊ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
የኢራን መንግስትም ድርጊቱ ከህዝብ ባህል እና ሞራል አንጻር ተቀባይነት የለውም በሚል ጥንዶቹ ንብረቶቻቸውን ለውሻቸው እንዲያወርሱ የረዳውን የንግድ ድርጅት ዘግታለች፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ሰዎች ንብረቶቻቸውን ለእንስሳት ሊያወርሱ የሚችሉበት ግልጽ ህግ የለም የተፈጸመው ድርጊትም ህገወጥ ነው ተብሏል፡፡
የኢራን ወግ አጥባቂ የሀይማኖት እና ባህል አስተማሪዎችም ዜጎች ውሻ ሊኖራቸው አይገባም ካላቸውም ወደ እንስሰት ማቆያ ሊያስገቡ ይገባል ማለታቸው ተገልጿል፡፡
የኢራን ዋና ከተማ የሐነችው ቴህራን ከተማ የቤት እንስሳትን ወደ አደባባይ ይዞ መውጣት እና መንቀሳቀስን ከልክላለች፡፡