ሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ከኢራን ተቀብላለች - ዋይትሀውስ
የቴህራንን ድሮኖች በሞስኮ ለመገጣጠም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ደርሰንበታል ብለዋል የዋይትሀውስ ቃል አቀባይ
አሜሪካ በኢራን ላይ ማዕቀቦችን ለመጣል መዘጋጀቷ ተገልጿል
የሩሲያ እና ኢራን ወታደራዊ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አሳስቦኛል ብላለች አሜሪካ።
ሩሲያ ከኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ተረክባ በዩክሬን ጦርነት እየተጠቀመች መሆኑንም ነው ያስታወቀችው።
የዋይትሀውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ የደህንነት መረጃዎችን ጠቅሰው እንደተናገሩት፥ ቴህራን በካስፒያን ባህር በኩል ነው ድሮኖቹን የላከችው።
"ሩሲያ የኢራን ድሮኖችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም መዘጋጀቷም አሳሳቢ ነው" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
በሩሲያ አላቡጋ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የድሮን መገጣጠሚያውን እየገነባች መሆኑን በሳተላይት ምስሎች አረጋግጠናልም ነው ያሉት።
ሩሲያ በበኩሏ ሚሳኤልና የአየር መቃወሚያዎችን ለኢራን መስጠቷንና ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ሄሊኮፕተርና ራዳሮችን ለማቅረብ ንግግር እያደረጉ መሆኑንም ኪርቢ ገልፀዋል።
ይህም ለዩክሬን ብሎም ለመላው አለም ሰላምና ደህንነት ስጋት እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።
ኢራን ለሩሲያ ድሮኖች መላኳ ከተገለፀ በኋላ አሜሪካ በቴህራን ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ሞስኮ የኢራን ድሮኖችን በዩክሬን ጦርነት መጠቀሟን እስካሁን ማረጋገጫ ባትሰጥም የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ማደጉ ዋሽንግተንን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል።
የዋይትሀውስ ቃልአቀባይ ጆን ኪርቢም የድሮን ዝውውሩ በኢራን ላይ የተጣሉ የመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀቦችን የተላለፈ ነው በሚል "አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ዝተዋል።