ኢራን ሁለተኛዋን ሳተላይት ወደ ህዋ አመጠቀች
ኢራን በሪቮሊሹናሪ ጋርድ በተሰራ ሮኬት አማካኝነት ሁለተኛዋን የምርምር ሳተላይት ባለፈው ቅዳሜ ወደ ህዋ ማምጠቋ ዘግቧል
ኢራን ሳተላይቷን ያመጠቀችው አሜሪካ በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ባለስቲክ ሚሳይል ለሩሲያ አስተላልፋለች የሚል ክስ ባቀረቡባት ወቅት ነው
ኢራን ሁለተኛዋን ሳተላይት ወደ ህዋ አመጠቀች።
ኢራን በሪቮሊሹናሪ ጋርድ በተሰራ ሮኬት አማካኝነት ሁለተኛዋን የምርምር ሳተላይት ባለፈው ቅዳሜ ወደ ህዋ ማምጠቋን የመንግስት መገናኛ ብዙኻንን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ኢራን ሳተላይቷን ያመጠቀችው አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ባለስቲክ ሚሳይል ለሩሲያ አስተላልፋለች የሚል ክስ ባቀረቡባት ወቅት ነው። ኢራን ይህን አስተባብላለች።
በቋይም-100 ሳተላይት ተሸካሚ ሮኬት ወደ ህዋ የተወነጨፈችው ቻምራን-1 ሳተላይት በ550 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ኦርቢት(ምህዋር) ላይ መቀመጧን እና ወደ መሬት ምልክት መላኳን ዘገባው ጠቅሷል። ሳይተላይቷን ለማስወንጨፍ ጥቅም ላይ የዋለው ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀመው ሮኬት በሪቮሉሽናሪ ጋርድ ኤሮስፔስ ክፍል ነው የተሰራው።
እንደዘገባው ከሆነ 60 ኪሎግራም የምትመዝነው የዚች ሳተላይት ዋና አላማ በኦሮቢት ላይ ለሚደረግ እንቅስቃሴ የሶፍትዌር እና የሀርድዌር ስርአቶችን መሞከር ነው ተብሏል።
ባለፈው ጥር ወር ኢራን ሶራያ የተባለች ሳተላይት 750 ኪሎሜትር በሚርቅ ኦርቢት ላይ ማስቀመጥ ችላ ነበር። ይህ ርቀት ለሀገሪቱ በጣም ከፍተኛ የሚባለው ነው።
የአሜሪካ ጦር ኢራን ሳይተላይቶችን ኦርቢት ላይ ለማስቀመጥ የረጅም ርቀት ባለስቲክ ሚሳይል ቴክኖሎጂ ሳትጠቀም አትቀርም የሚል ጥርጣሬ አለው። ጦሩ ኢራን ቴክኖሎጂውን የኑክሌር ጦር መሳሪያን ጨምሮ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን ለማስወንጨፍ ልትጠቀምበት ትችላለችም ብሏል።
ኢራን ግን የሳተላይት እንቅስቃሴዋ ከባለስቲክ ሚሳይል ልማት ጋር አይያያዝም ስትል አስተባብላለች።
በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ የሚሳይል ፕሮግራም ካላቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢራን በቴክኒክ ችግር ምክንያት በቅርብ አመታት ውስጥ ያስወነጨፈቻቸው ሳተላይቶች ከሽፈዋል።