ሰሜን ኮሪያና ሩሲያ የጋራ ፍላጎታቸውን የሚያደናቅፉ አካላትን በጋራ ለመመከት ተስማሙ
የሩሲያው የጸጥታ ምክርቤት ዋና ጸሃፊ ሰርጌ ሾጉ በፒዮንግያንግ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር መክረዋል
ዩክሬን እና አሜሪካ፥ ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ ሮኬቶችና ሚሳኤሎችን እየላከች ነው ሲሉ ይከሳሉ
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ።
የሩሲያው የጸጥታ ምክርቤት ዋና ጸሃፊ ሰርጌ ሾጉ በፒዮንግያንግ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር የሁለቱን ሀገራት ትብብር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ኪም እና የቀድሞው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሾጉ በወቅታዊ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች መምከራቸውንም ነው ኬሲኤንኤ የዘገበው።
በውይይቱ የሞስኮ እና ፒዮንግያንግን “የጋራ ፍላጎት የሚጎዱ ነገሮችን በትብብር ለመመከት” ተስማምተዋል ተብሏል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገራቱ ትስስር በተፈራረሙት ስትራቴጂካዊ ትብብር ስምምነት መሰረት እያደገ እንዲሄድ ፒዮንግያንግ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
የሩሲያን ልኡክ እየመሩ በትናንትናው እለት ፒዮንግያንግ የገቡት ሰርጌ ሾጉ በሀምሌ ወር ያደረጉት ጉብኝት የሩሲያና ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ትብብር እያደገ መሄዱን አመላካች እንደነበር የሬውተርስ ዘገባ ያወሳል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በሰኔ ወር በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ሲያደርጉ ከፒዮንግያንግ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው መገለጹ አይዘነጋም።
ሩሲያ በዩክሬን አሜሪካ መራሽ የኔቶ የእጅ አዙር ጦርነት እንደተከፈተባት ታምናለች።
ሰሜን ኮሪያም ዋሽንግተን ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ጋር በመተባበር በቀጠናው ውጥረት እየፈጠረች ነው ስትል ትከሳለች።
አሜሪካ የጋራ ስጋታቸው አድርገው የሚመለከቱት ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትብብራቸው ይህንኑ ስጋት የመመከት አላማ እንዳለው ይገልጻሉ።
ዋሽንግተን እና አጋሯ ኬቭ ደግሞ ይህን ትብብር ይቃወምታል፤ ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ ሮኬቶችና ሚሳኤሎችን እየላከች ኬቭን እየደበደበች ነው ሲሉም ይከሳሉ።
ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ግን ክሱን ውድቅ በማድረግ ወታደራዊ ትብብራቸውን ቀጥለዋል።