ባይደን በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ሊያደርጉ ነው
ፕሬዝዳንቱ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት የተራዘመውን የአንጎላ ጉብኝታቸውን በቀጣይ ሳምንታት ያደርጋሉ ተብሏል
ቻይና በአፍሪካ የምታካሂደው ኢንቨስትመንት እየጨመረ መሄድ ዋሽንግተንን አሳስቧል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ሊያደርጉ ነው።
ባይደን በቀጣይ ሳምንታት አንጎላን እንደሚጎበኙ ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የፕሬዝዳንቱ የአንጎላ ጉብኝት ከመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ እና ከህዳሩ ወር ፕሬዛድንታዊ ምርጫ በፊት ባለው ጊዜ እንደሚሆን ነው የተነገረው።
ዋይትሃውስ ግን ስለፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ጉብኝት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ባይደን ከ2015 በኋላ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ሀገራትን የጎበኙ የአሜሪካ መሪ ይሆናሉ። ከዘጠኝ አመት በፊት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ እና ኬንያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ መሪዎች ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ህዝብ ያላትን አፍሪካን አይጎበኙም፤ ከጎበኙም በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ነው የሚል ትችት ይነሳባቸዋል።
አወዛጋቢው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካን የዘለፉበት ንግግራቸውም የአፍሪካ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ጥላ ማጥላቱ ነው የሚነገረው፡፡
በ2021 ስልጣን የያዙት ጆ ባይደንም በታህሳስ ወር በዋሽንግተን የአፍሪካ መሪዎችን ጋብዘው ከመምከር በዘለለ እንደ ቤጂንግ ለአህጉሪቱ ትኩረት የሰጠ እንቅስቃሴ አላደረጉም በሚል ይተቻሉ።
ፕሬዝዳንት ባይደን በነዳጅ የበለጸገችውን አንጎላ ለመጎብኘት ያቀዱት ባለፈው አመት ቢሆንም በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት መራዘሙ ተገልጿል።
አንጎላን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በባቡር የሚያስተሳስር ፕሮጀክትን በገንዘብ የደገፈችው አሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትሯን ሊዩድ ኦስቲን ባለፈው አመት ልካ ነበር።
ቀጣዩ የባይደን ጉብኝትም የቤጂንግን የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መግታት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች እንደሚካሄዱበት ይጠበቃል።