ኢራን ከቀይ ባህር ውጪ ተጨማሪ የዓለም ባህር ትራንስፖርት መስመር አቋርጣለሁ አለች
በህንድ ውቂያኖስ ላይ ይጓዝ የነበረን መርከብን ተኩሳ መምታቷ ተገለጸ
አሜሪካ ቀይ ባህርን ከየመን አማጺያን ለመጠበቅ የጋራ ጥምር ጦር ማቋቋሟ ይታወሳል
ኢራን ከቀይ ባህር ውጪ ተጨማሪ የዓለም ባህር ትራንስፖርት መስመር አቋርጣለሁ አለች፡፡
ለፍልስጤም ነጻነት እንደሚታገል የሚገልጸው ሐማስ ከ80 ቀን በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከባድ ጦርነት መከሰቱ ይታወሳል፡፡
ይህ ጦርነት ከ20 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን እና ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላዊያን እንዲገደሉ ምክንያት ከመሆኑ ባለፈ የቀይ ባህር ትራንስፖርት ንግድን አስተጓጉሏል፡፡
ከሰሞኑ የየመን ሁቲ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በቀይ ባህር በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁን ደግሞ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ግፊት በማድረግ ላይ የምትገኘው ኢራን መነሻውን ሳውዲ አረቢያ አድርጎ ወደ ሕንድ በመጓዝ ላይ የነበረ መርከብን በሰው አልባ አውሮፕላን እንደመታች ተገልጿል፡፡
ቢቢሲ የአሜሪካ ጦርን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው መርከቡ ኬሚካል ጭኖ በመጓዝ ላይ እያለ በደረሰበት ጥቃት የከፋ ጉዳት አልደረሰም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የሁቲ ታጣቂዎችም በተመሳሳይ ሁለት ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ተኩሰው ዓለም አቀፉን የባህር ትራንስፖርት መስመር እንዳስተጓጎሉ ተገልጿል፡፡
ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት የተመታ መርከብ ባይኖርም የንግድ መስመሩን የበለጠ ለአደጋ ስለማጋለጣቸው አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እነዚሁ የየመን ሁቲ አማጺያን አራት ሰው አልባ አውሮፕላን ወደ ቀይ ባህር ለተጨማሪ ጥቃት ያሰማሩ ቢሆንም በአሜሪካ መክሸፋቸው ተገልጿል፡፡
ይሁንና አማጺያኑ በደቡባዊ ቀይ ባህር መስመር ባደረሱት ጥቃት ነዳጅ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ መርከብ በድሮን ጥቃት ሲመታ አንድ ተመሳሳይ መርከብ ደግሞ ለጥቂት ከጥቃቱ አምልጧል ተብሏል፡፡
ኢራን በበኩሏ በአሜሪካ ስለቀረበባት ክስ እስካሁን ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም አሳስባለች፡፡
የእስራኤል ጥቃት በጋዛ የሚቀጥል ከሆነ እና አሜሪካ ድጋፏን የማታቆም ከሆነ ከቀይ ባህር ባለፈ ተጨማሪ የዓለም ባህር ትራንስፖርት መስመርም ሊስተጓጎል ይችላል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡
በቀይ ባህር ትራንስፖርት አደጋ ማንዣበቡን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ የሎጅስቲክስ ተቋማት አገልግሎታቸውን በማቋረጥ ላይ ናቸው፡፡
አሜሪካ የቀይ ባህር ትራንስፖርት ከተደቀነበት ቀውስ ለመታደግ በሚል በርካታ ሀገራትን ያሳተፈ የባህር ሀይል ጦር ማዋቀሯን አስታውቃለች፡፡