የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባህር የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያጠናክር ዛተ
ቡድኑ አሜሪካ በቀይ ባህር የጋራ ግብረሃይል ብታሰማራም በእስራኤል መርከቦች ላይ በየ12 ስአቱ ጥቃት አደርሳለሁ ብሏል
የቀይ ባህር ደህንነት አሳሳቢ መሆን በነዳጅና ሸቀጦች ዋጋ ላይ ተጽዕኖው እንዳይበረታ ተሰግቷል
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሀውቲ በቀይ ባህር በሚጓዙ የእስራኤል መርከቦች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ አሳሰበ።
ቡድኑ ባወጣው መግለጫ በየ12 ስአቱ በእስራኤል መርከቦች ላይ የሮኬትና ድሮን ጥቃት እንደሚፈጽም ነው ያስታወቀው።
እስራኤል በጋዛ በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ካላቆመች ጥቃቱ እንደማቆምም ዝቷል።
የሃውቲ ታጣቂዎች አሜሪካ መሩ የቀይ ባህር የጋራ ግብረሃይል ጥቃቶቹን ለማክሸፍ በይፋ ቢሰማራም በእስራኤል መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሱን እንደሚገፋበት ማሳሰቡንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የቡድኑ ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ መሄድ የተለያዩ የመርከብ ኩባንያዎች ቀይ ባህርን እንዲሸሹ አድርጓል።
በስዊዝ ካናል በኩል የሚያደርጉትን ጉዞ ለውጠው በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ መጓዝ የጀመሩ መርከቦች እንዳሉም ነው ቢቢሲ የዘገበው።
ለአብነት ከታይዋን ኔዘርላንድስ በቀይ ባህር በኩል 18 ሺህ 500 ኪሎሜትር ይረዝማል፤ 25 ቀን ተኩልም ይወስዳል። በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ግን 25 ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝም ሲሆን 34 ቀናትን ይፈጃል።
የአለማችን 10 በመቶ የወጪ ንግድ የሚተላለፍበት ቀይ ባህር ደህንነት መታወክ የአለም የነዳጅና የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ሊያደርግ እንደሚችል ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው።
እስራኤል በበኩሏ በጋዛ የምትፈጸምውን ጥቃት እያጠናከረች መሄዱን መርጣለች።
ንጹሃንን መጠበቅ ያልቻለ ወታደራዊ ዘመቻ እያደረጉ ነው በሚል አለማቀፍ ጫናው የበረታባቸው ቤንያሚን ኔታንያሁም ቀሪዎቹ (129) ታጋቾች እስካልተለቀቁና ሃማስ ካልተደመሰሰ የሚቆም ጦርነት የለም ብለዋል።
ሃማስም ለ11 ሳምንት ከእስራኤል ከፍተኛ ጥቃት ቢሰነዘርበትም በቴል አቪቭ የሮኬት ጥቃት ከማድረስ ያገደኝ ሃይል የለም ብሏል።
በቴል አቪቭ በፈጸመው ጥቃት የደረሰው ጉዳት ባይገለጽም የማስጠንቀቂያ ደወል መሰማቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው 74ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 19 ሺህ 667 ደርሷል።