ኢራን በዩክሬን አይሮፕላን መከስከስ የተቃጣባትን ክስ ተቃወመች
ባለፈው ረቡዕ ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ተከስክሶ የ176 ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የአይሮፕላን አደጋ የኢራን እጅ አለበት የሚለውን ክስ ኢራን እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡
የአደጋውን መንስኤም አሜሪካ እንድታጣራ ኢራን ጥሪ አቅርባለች፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው ጥሪው የደረሰው የአሜሪካው የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ጥያቄውን ተቀብሎ አጣሪ ቡድን እንደሚመድብ አሳውቋል፡፡
የተለያዩ ሀገራት ኢራን በተኮሰችው ሚሳይል አይሮፕላኑ ተመቶ ሳይወድቅ እንዳልቀረ ግምታቸውን የገለጹ ሲሆን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃንም ከደህንነት ተቋማት ያገኘነው መረጃ አይሮፕላኑ ተመቶ መውደቁን ያሳያል ብለው በሰፊው ዘግበዋል፡፡
በዛሬው እለት ደግሞ አይሮፕላኑ ሲመታ ያሳያሉ የተባሉ የቪዲዮ ማስረጃዎችም ተለቀዋል፡፡
ይሁንና የሚወጡ መረጃዎች ሁሉ በኢራን ላይ የተከፈቱ የስነልቦና ጦርነቶች ናቸው እንጂ እውነት አይደሉም በሚል ኢራን አስተባብላለች፡፡ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ያሏቸው ሀገራትም ተወካዮቻቸውን ልከው ከቦይንግ ጋር በጋራ የጥቁር ሳጥኑን መረጃ እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ተቋም አውሮፕላኑ ከመነሳቱ ከሁለት ቀናት በፊት ፍተሻ የተደረገለት ቢሆንም የቴክኒክ ችግር ስለገጠመው ተከስክሷል ብሏል፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ