ለሃኒየህ ግድያ የአጻፋ እርምጃ ያልወሰድነው የእስራኤልን ቀጠናዊ ግጭት የመቀስቀስ ፍላጎት ለማምከን ነው - የኢራኑ ፕሬዝዳንት
ይህ ማለት ግን "በአስፈላጊው ሰአትና ሁኔታ ለተቃጣብን ጥቃት የምንሰጠውን የአጸፋ ምላሽ ትተነዋል ማለት አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል
ፕሬዝዳንቱ በቀጠናዊ እና አለማቀፍ ጉዳዮች ለቀረበላቸው ጥያቂዎች ምላሽ ሰጥተዋል
እስራል ከሀማስ ጋር እያደረገች ያለው ጦርነት የመጨረሻ ግብ ቀጠናዊ ጦርነትን ማስከተል መሆኑን የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዚሽኪን ተናገሩ፡፡
የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ግድያን ተከትሎ ኢራን እስካሁን የአጸፋ ምላሽ ከመስጠት የተቆጠበችው እስራኤል ወደ ቀጠናዊ ጦርነት ልትጎትተን እንደምትፈልግ ስለምናውቅ ነው ብለዋል፡፡
ከሶስት ወራት በፊት የኢራን ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ፔዚሽኪያን ለሁለት ሰአት ተኩል በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ የተለያዩ ቀጠናዊ እና ሀገራዊ ሁኔታዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ “እስራኤል በቀጠናው እያደረገች ያለው ነገር በኢራን የእስማኤል ሀኒየህ ግድያ እና የጋዛው ጦርነት ግጭት ለመቀስቀስ በማሰብ እንደሚደረግ እናውቃለን፤ ለዚያም ነው እስካሁን ጥቃት ከመሰንዘር የተቆጠብነው ነገር ግን በአስፈላጊው ሰአት እና ሁኔታ ለተቃጣብን ጥቃት የምንሰጠውን የአጸፋ ምላሽ ትተነዋል ማለት አይደለም” ብለዋል፡፡
የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም የእስራኤል ዋነኛ አጋር ናት የሚባልላት አሜሪካ ለዘብተኛ አቋም ማሳየቷን እና ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ጥርጣሬ እንዳለቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ኢራን ለሩስያ የመካከለኛ እና የአጭር ርቀት ባላስቲክ ሚሳኤሎችን እየሸጠች እንደምትገኝ በዋሽንግተን በተደጋጋሚ ለሚቀርበው ክስ በሰጡት ምላሽ፤ እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ አንስቶ ለሞስኮ ምንም አይነት የጦር መሳርያ እንዳልተሸጠ እና ከእርሳቸው በፊት በነበሩ አመራሮች ስለተፈጸሙ ስምምነቶች ሀሳብ መስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ቢሉም በነሀሴ ወር እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የጦር መሳርያ ስምምነት መፈጸሙን እና ባሳለፍነው ሳምንት የጦር መሳርያዎች ወደ ሩስያ መላካቸውን የምእራባውያን የደህንነት መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ለየመን ሀውቲ ታጣቂዎች ኢራን የሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ድጋፍ ስለማድረጓ ተጠይቀው “ድጋፍ እናድርግ እንኳን ብንል ከኢራን የመን አይደለም ሚሳኤል ሰው ለማጓጓዝ እንኳን ከባድ ነው” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ከትላንት በስቲያ ሀውቲዎች ያስወነጨፉት የሀይፐርሶኒክ ሚሳኤል በማዕከላዊ እስራኤል ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡
ለዘብተኛ አቋም እንዳላቸው የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ከምእራብውያን ጋር ሀገራቸው ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ይፈልጋሉ፡፡
ወደ ስልጣን ሲመጡ ቃል ከገቡባቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከልም ለቴሄራን ኢኮኖሚ መድቀቅ ምክንያት የሆነውን በኒዩክሌር ጉዳይ የተጣለውን ማእቀብ አስነሳለሁ ማለታቸው ይጠቀሳል፡፡