የእስራኤል ጦር ለጋዛው ጦርነት አፍሪካውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን እየመለመለ ነው ተባለ
ጥገኝነት ጠያቂዎቹ የእስራኤል ጦርን ተቀላቅለው ካገለገሉ በእስራኤል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸውም ነው የተገለጸው
በእስራኤል 30 ሺህ የሚጠጉ በአብዛኛው የኤርትራ እና ሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎች ይገኛሉ
የእስራኤል ጦር ለጋዛው ጦርነት አፍሪካውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን እየመለመለ መሆኑ ተገለጸ።
የሀገሪቱ ወታደራዊ ምንጮች ምልመላው እስካሁን በይፋ ባይገለጽም እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠውልኛል ብሏል ሃሬትዝ ጋዜጣ።
ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ፈቃደኛ ሆነው የሁለት ሳምንት ስልጠና ወስደው ወደ ጋዛ ካቀኑ በእስራኤል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚያገኙ ቃል እንደተገባላቸውም ነው ዘገባው የጠቆመው።
በእስራኤል ከ30 ሺህ በላይ በአብዛኛው የኤርትራ እና ሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደሚገኙ በእስራኤል የስደተኞች መብት ተሟጋች ተቋሙ “ሆትላይን ፎር ረፊዩጂስ ኤንድ ሚግራንትስ” መረጃ ያሳያል።
ከጥገኝነት ጠያቂዎቹ ውስጥ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የተሰጣቸው ግን ከ1 ከመቶ በታች መሆናቸውን በተቋሙ የፐብሊክ ፖሊሲ ዳይሬክተሩ ሺራ አቦ ተናግረዋል።
በሃማስ የጥቅምት 7ቱ ጥቃት ህይወታቸው ካለፈ ከ1 ሺህ 100 በላይ ሰዎች ሶስቱ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደነበሩ የሚያወሳው ሃሬትዝ፥ ጥቃቱ በእስራኤል የሚገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በጋዛው ጦርነት እንሳተፍ የሚል ጥያቄ እንዲያቀርቡ ማድረጉን ይገልጻል።
የእስራኤል ወታደራዊ አመራሮችም ጥገኝነት ጠያቂዎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ በጦርነቱ እንዲሳተፉ ሲመለምል መቆየቱን ዋቢዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገና በ16 አመቱ ወደ እስራኤል መግባቱን የገለጸ ጥገኝነት ጠያቂ የጋዛው ጦርነት እንደተጀመረ ከአንድ የፖሊስ አዛዥ የስልክ ጥሪ እንደደረሰው ተናግሯል።
“የእስራኤል ጦርን መቀላቀል ያለባቸውን ልዩ ሰዎች እየፈለጉ መሆኑን ነገሩኝ፤ (የጋዛው ጦርነት) ለእስራኤል ህይወት ወይም ሞት መሆኑንም ገለጹልኝ” ሲልም ለሃሬትዝ ገልጿል።
ከስልክ ጥሪው በኋላ ከተለያዩ አመራሮች ጋር በመገናኘት ከሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር የሁለት ሳምንት ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ከእስራኤል መንግስት ህጋዊ ሰነድ እንደሚሰጠው መነገሩንም አብራርቷል።
በእስራኤል የስደተኞች መብት ተሟጋች ተቋሙ “ሆትላይን ፎር ረፊዩጂስ ኤንድ ሚግራንትስ” ግን ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያገኙት ጥቅም በወሬ ደረጃ ይነገር እንጂ በግልጽ እና በይፋ እስካሁን አልተገለጸም ብሏል።
በውትድርና ተመልምለው ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዳሉ የደረሰው ምንም መረጃ እንደሌለም በመጥቀስ።
ተቋሙ ከሀገራቸው ጦርነትና ግጭትን ሸሽተው የመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በጥቅም በማባበል ለውትድርና መመልመል ከአለማቀፍ ህግ የተቃረነ መሆኑን ገልጿል።
የእስራኤልን ጦር መቀላቀል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ አግባብነት የለውም ሲልም ተቃውሞውን አሰምቷል።
የእስራኤል የመከላከያ ምንጮች ግን የጥገኝነት ጠያቂዎቹ የውትድርና ምልመላ ከሀገሪቱ ህግ የሚቃረን አለመሆኑን ለሃሬትዝ ተናግረዋል።