ኢራን ሄዝቦላ የፈጸመው ጥቃት እስራኤል የመከላከል አቅሟን እንዳጣች የሚያሳይ ነው አለች
እስራኤል እና ሊባኖስ በ10 ወራት ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ በቤሩት፣ የሀማስ የፖለቲካ መሪ በቴህራን መገደላቸውን ተከትሎ ነው
ኢራን ሄዝቦላ የፈጸመው ጥቃት እስራኤል የመከላከል አቅሟን እንዳጣች የሚያሳይ ነው አለች።
ሄዝቦላ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል የመከላከል አቅሟን ማጣቷን እና በቀጣናው ያለው ስትራቴጂካዊ የኃይል ሚዛን መቀየሩን ኢራን በዛሬው እለት ገልጻለች።
ሄዝቦላ እሁድ እለት ጠዋት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈ ሲሆን የእስራኤል ጦርም ጥቃቱን ለማክሸፍ ሊባኖስን በ100 ጄቾች መምታቱን ገልጿል። ይህ የተኩስ ልውውጥ የድንበር ግጭት ከተጀመረ ከ10 ወራት ወዲህ ከፍተኛ የሚባል ግጭት ነው።
" እስራኤል እንደ አሜሪካ ካሉ ሀገራት ሙሉ ድጋፍ ብታገኝም፣ ጥቃት የሚደርስባትን ጊዜ እና ቦታ መተንበይ አትችልም " ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናሰር ከናኒ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ከናኒ አክለውም በቀጣናው ያለው አሰላለፍ ለእስራኤል በማይጠቅም መልኩ እየተቀየረ ስለሆነ አሁን ላይ እስራኤል "በወረራ በያዘቻቸው ግዛቶች ውስጥ ራሷን እየተከላከለች" ነው ብለዋል።
ከጋዛው ጦርነት በተጓዳኝ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ የሄዝቦላ አጋር የሆነችውን ኪራንን እና የእስራኤልን ዋና አጋር ወደ ግጭት ሊያስገባቸው ይችላል።
የሄዝቦላ መሪ የሆነው ሰይድ ሀሰን ነስረላህ እንደተናገረው ባለፈው ወር የተፈጸመውን የቡድኑን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ፉአድ ሹክር ግድያን ለመበቀል የሰነነዘረው ጥቃት በታቀደው መልኩ ተጠናቋል።
እስራኤል እና ሄዝቦላ ሰሞኑን በፈጸሙት የተኩስ ልውውጥ ሶስት በሊባኖስ እና አንድ በእስራኤል ሞት ያስከተለ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች አሁን ላይ ግጭቱን እንዳይባባስ እንደሚፈልጉ አመላክተዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ በቤሩት፣ የሀማስ የፖለቲካ መሪ በቴህራን መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
ለግድያዎቹ እስራኤልን ተጠያቂ ያደረጉት ሀማስ እና ኢራን እስራኤልን እንደሚበቀሉ ሲዝቱ ቆይተዋል።