የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሁሉም አባላቱ የትኛውንም አይነት የኮሙዪኒኬሽን መሳሪያ መጠቀም እንዲያቆሙ አዘዘ
ኢራን ውሳኔውን ያሳለፈችው በሄዝቦላህ አባላት የሬዲዮና የፔጀር መገናኛዎች ፍንዳታን ተከትሎ ነው
በሄዝቦላህ አባላት እጅ የፈነዱ የፔጀርና የሬዲዮ መገናኛዎች ናሙና ለምርምር ወደ ቴህራን ተልከዋል
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሁሉም አባላቱ የትኛውንም አይነት የኮሙዪኒኬሽን መሳሪያ መጠቀም እንዲያቆሙ ማዘዙን የደህነነት ባለስልጣናት አስታወቁ።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ውሳኔውን ያሳለፈው በሊባኖሱ የሄዝቦላህ አባላት አባላት የሬዲዮና የፔጀር መገናኛዎች ላይ የደረሰው ፍንዳታ በርካቶችን መግደሉን ተከትሎ እንደሆነም ሁለት የኢራን የደህንነት ባለስልጣናት ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የደህነነት የመረጃ ምንጮቹ እንደተናሩት ከሆነ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የኮሙዪኒኬሽን መሳሪያዎችን ጨምሮ ባሉት ሁሉም መሳሪያዎች ላይ ከፍተኛ ፍተሻ እያደረገ ይገኛል።
አሁን ላይ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባላት የፔጀር እና የሬዲዮ መገናኛዎችን መጠቀም አቁመሻ ያሉት የደህንነት ባስልጣናቱ፤ ነገር ግን 190 ሺህ አብዮታዊ ዘብ አባላቱ በምን አይነት መገናኛ ዘዴ ይጠቀማሉ የሚለው ላይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አሁን ላይ ደህነንቱ የተጠበቀ የመልእክት መለዋወጫ ዘዴ ብቻ ነው የምንጠቀመው ሲሉም አስታውቀዋል።
በሄዝቦላህ አባላት እጅ የፈነዱ የፔጀር እና የሬዲዮ መገናኛዎች ውስጥ የተወሰኑት ለምርምር ወደ ቴህራን መላካቸውንም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በብዛት የሚጠቀማቸው የጦር እና የደህንነት መሳሪያዎች አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥ የተመረቱ ቢሆኑም፤ ከቻይና እና ከሩሲያም መሳሪያዎችን እንደሚያስገባም ተናግረዋል።
ኢራን ሰርጎ ገብ የእስራኤል ሰላዮች ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነባትም የደህንነት ባለስልጣኑቱ አክለው የተናገሩ ሲሆን፤ ይህን ለማጣራት ኢራን በአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛና መከከለኛ አመራሮች እንቅስቃሴን እየመረመረች መሆኑ ተነግሯል።
ምርመራውም በኢራን ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ያላቸውን የባንክ ሂሳቦች እንዲሁም የጉዞ ታሪካቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ ያካትታል" ሲሉ የደህንነት ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስቴሮች የደህንነት ባለስልጣናት ለሮይተርስ በሰጡት አስተያየትዙሪያ ምላሽ አልሰጡም።
ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ እና ረቡዕ በሊባኖስ የሄዝቦላህ አባላት የፔጀር እና የሬዲዮ መገናኛዎች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት በደረሰ ፍንዳታ 39 ሰዎች ሲሞቱ ከ3,000 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከተቀነባበረው ጥቃት ጀርባ እስራኤል አለች ያለ ሲሆን፤ ኢስራኤል በጉዳዩ ላይ እስካን ዝምታን መርጣለች።