በጋዛው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንደምትታቀብ አስታወቀች
በነገው እለት በኳታር ወይም ግብጽ በሀማስ አና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ድርድር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል
ኢራን ምን ያህል ጊዜ እንደምትታገስ ይፋ ባታደርግም የተኩስ አቁም ስምምነት የሚፈጸም ከሆነ በእስራኤል ላይ ጥቃት እንደማትሰነዝር አስታውቃለች
ኢራን የጋዛው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚፈጸም ከሆነ በእስራኤል ላይ እሰነዝረዋለሁ ያለችውን የአጸፋ ምላሽ እንደምታጤነው አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ የደህንነት ተቋም ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ቴልአቪቭ በኢራን ሉአላዊ ክልል ውስጥ በመግባት ለፈጸመችው ወንጀል ማካካሻው የተኩስ አቁም ስምምነት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ ግድያን ተከትሎ ቴሄራን በአይነቱ ከፍተኛ የተባለ ቀጥተኛ ጥቃት በእስራኤል ላይ እንደምትፈጽም ለሳምንታት ስትዝት ቆይታለች፡፡
የደህንነት ባለስልጣኑ ኢራን ከቀጠናው አጋሮቿ ጋር በመሆን ለተፈጸመው ጥፋት ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አድርጋ ማጠናቀቋን አስታውቀዋል፡፡
በነገው እለት በኳታር ወይም በግብጽ በሀማስ እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይሁንና ኢራን የአጸፋ ምላሽ ከመስጠቷ በፊት ለድርድሩ ሂደት ምን ያህል ጊዜ እንደምትታገስ በይፋ አላሳወቀችም፡፡
የነጩ ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ጆን ኪርባይ በዚህ ሳምንት ኢራን የዛተችውን ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል የደህንነት መረጃዎች ማመላከታቸውን በትላንትናው እለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
አክለውም የአጸፋ ምላሹ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመካሄዱ ወይም ውጤቱ ከመታወቁ በፊት የሚደረግ ከሆነ የድርድር ሂደቱ ላይ ጥላ እንደሚያጠላ ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
የእስራኤል የመከላከያ ሚንስትር ዮቭ ጋለንት በበኩላቸው በቴሄራን እና በቤሩት የሚገኙ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተልን ነው፤ ጥቃት ሊሰነዘር የሚችለበትን ሁኔታ እና ኢላማ ላይ ቅድም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡
በቅርብ ሳምንታት በቀጠናው እያየለ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ አሜሪካ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ስትሆን ቱርክን ጨምሮ ሶስት የአካባቢው ሀገራት ቴሄራን ውጥረቱን ከሚያባበስ የአጸፋ ምላሽ እንድትታቀብ እንዲያግባቡ ሀላፊነት ሰጥታለች፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ኢራን በዚህ የአጸፋ ምላሽ ማስፈራርያ የጋዛውን ጦርነት ማስቆም የምትችል ከሆነ ከፍተኛ ድል የሚጎናጽፋት ነው። ሆኖም ይህ የማይሳካ ከሆነ ቀጠናዊ ግጭት እንዲቀሰቀስ ባትፈልግም በቴልአቪቭ ላይ ጥቃት ከመሰንዘር ወደ ኋላ አትልም፡፡
ከዚህ ባለፈም ኢራን በድርድር ሂደት ላይ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የጎንዮሽ ስብሰባዎች እና የዲፕሎማሲ ጥረቶች ላይ ተሳትፎ እንዲኖራት ትፈልጋለች ተብሏል፡፡
በትላንትናው እለት አሜሪካ ፣ ብሪታንያ ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን ጥቃት ከመሰንዘር እንድትታቀብ ጥሪ ቢያቀርቡም ተሄራን ጥሪውን ሳትቀበለው ቀርታለች፡፡