ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ ተገለጸ
ቱርክ እና የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሻሻሎች መኖራቸውን አመላክተዋል።
ሶስተኛው ዙር ድርድር በፈረንጆቹ መስከረም 17 እንደሚካሄድ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል
ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት ጉዳይ በቱርክ አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ቱርክ እና የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሻሻሎች መኖራቸውን አመላክተዋል።
በቱርክ አንካራ የተካሄደው ድርድር፣ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ጥር አንድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ለንግድ እና ለባህር ኃይል ሰፈር የሚሆን 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ለማግኘት እና በምላሹ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት እንደተስማማች ከተገለጸ በኋላ የተበላሸውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለመጠገን ያለመ ነው።
ሶማሊላንድን የራሷ ግዛት አካል አድርጋ የምታየው ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው ስምምነት ሉአላዊነቷን እና አለምአቀፍ ህግን የሚጥስ ነው በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምታለች።
ስምምነቱን ህገወጥ ነው ያለችው ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር በማባረር ምላሽ ሰጥታለች። ሶማሊያ አልሸባብን በመዋጋት ሲረዷት የነበሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ በሀገሪቱ የሰፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ለማስወጣት እየዛች ነው።
በቱርክ የተገኙት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ቀጥተኛ ያልሆነ ነበር። የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ሁለቱንም ለብቻ በማግኘት ነበር ድርድሩ እንዲካሄድ የተደረገው።
ፊዳን በሰጡት መግለጫ በሁለተኛው ዙር ድርድር ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን እና አሁን ላይ "በትላልቅ መርሆች ላይ መቀራረብ" አለ ብለዋል።
"ይህ ትርጉም ያለው መሻሻል" ነው ያሉት ፊዳን በፈረንጆቹ በመስከረም 17 የሚጀመረው ሶስተኛው ዙር ድርድር በሁለቱ ሀገራት መካከል "ዘላቂ እና ተጨባጭ" ስምምነት እንዲደረስ የማድረግ አላማ እንዳለው ገልጸዋል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ አህመድ መሻሻሎች መኖራቸውን እና የሞቃዲሹ መንግስት አለምአቀፍ ህግን እና የተመድን የውሃ ህግ መሰረት ያደረገ ስምምነት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
"ለሶስተኛ ዙር ስንዘጋጅ አሁን ያለው መሻሻል የመጨረሻ መፍትሄ ላይ ያደርሰናል በሚል ተስፋ ነው" ብለዋል አህመድ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ ሀገራቸው "ልዩነታችንን ለመፍታት እና ወደ መደበኛ ግንኘነት ለመመለስ ቀጣይነት ያለው ንግግር ለማድረግ" እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
ቱርክ ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ ጋር ቅርብ የሚባል ግንኙት አላት። ቱርክ የሶማሊያ ወታደሮችን የምታሰለጥን እና የልማት ድጋፍ የምታደርግ ሲሆን በምትኩ ቀልፍ በሆነው አለምአቀፍ የንግድ መስመር እግሯን መትከል ችላለች።
ቱርክ የማደራደር ጥረቷን የጀመረችው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ግንቦት ወር አንካራን በጎበኙበት ወቅት ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች በኋላ መሆኑን ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።