ኬንያዊቷ አትሌት በሶስት ተከታታይ ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ ሰራች
ኪፒይጎን ሩጫውን 3:51.29 ደቂቃ በማጠናቀቅ የኦሎምፒክን ሪከርድ መስበር ችላለች
ኪፒይጎን በተከታታይ በተካሄዱ ሶስት ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የምንግዜም ምርጥ ከሚባሉት የመካከለኛ ርቀት አትሌቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች
ኬንያዊቷ አትሌት በሶስት ተከታታይ ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ ሰራች።
ባለፈው ቅዳሜ በፓሪስ ኦሎምፒክ የ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር ያሸነፈችው ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፒይጎን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷል።
አትሌቷ በተከታታይ በተካሄዱ ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ ስታመጣ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ኪፒይጎን በተከታታይ በተካሄዱ ሶስት ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የመጀመሪያዋ እና የምንግዜም ምርጥ ከሚባሉት የመካከለኛ ርቀት አትሌቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች።
በውድድሩ የአውስትራሊያዋ ጀሲካ ሁል እና የእንግሊዟ ጆርጂያ ቤል በተከታታይ የብር እና የነሀስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
ኪፒይጎን ሩጫውን 3:51.29 ደቂቃ በማጠናቀቅ የኦሎምፒክን ሪከርድ መስበር ችላለች።
"በራሴ የተያዘውን ሪከርድ ለመጠበቅ እፈልግ ነበር፤ ህልም ነበረኝ። ለእኔ ገርሞኛል፤ አሳክቸዋለሁ። በጣም...በጣም ደስተኛ ነኝ" ስትል ለጋዜጠኞች ተናግራለች። "ታሪክ ለመስራት እጥር ነበር። አደረግሁት።"
የኪፐይጎን አንጸባራቂ የሩጫ ልምድ እዚህ የደረሰው አልጋ ባልጋ አልነበረም። በኬንያ በስምጥ ሸለቆ የተወለደችው እና ለቤተሰቦቿ ስምንተኛ ልጅ የሆነችው አትሌቷ፣ የ16 አመት ታዳጊ እያለች ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የሀገር አቋራጭ ውድድሩ በባዶ እግሯ ሮጣ አራተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላ ነበር።
ተሰጥኦ እንዳላት እና ሩጫ ህይወቷን ሊቀይር እንደሚችል የተረዳችው ኪፒይጎን ወደ ሩጫው በማተኮር በ30 አመቷ ስድስት የአለም ሻምፒዮንሽፕ እና አራት የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች።
የቅዳሜው ድል በ5000 ሜትር ውድድር ለጥቂት የብር ሜዳሊያ ያመለጣትን አትሌት የካሰ ነው። ኪፒይጎን ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ጋር ባደረገችው መገፋፋት ምክንያት ከውድድሩ ውጭ ተደርጋ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ ውሳኔው ተሽሯል።
"በ5000 ሜትር ውድድር ካጋጠመኝ ችግር በኋላ ዛሬ(በቅዳሜው ውድድር) ጠንክሬ እወጣለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር" ስልት ተናግራለች ኪፒይጎን።
በኦሎምፒክ መድረክ በሚካሄዱ የመካከለኛ ርቀት ሩጫ የበላይነት ይዘው ያጠናቅቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድሮ አልተሳካላቸውም። ነገርግን በማራቶን ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች ወርቅ እና ብር አስገኝተዋል።