የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ በባህረ ሰላጤው የንግድ መርከብን ተቆጣጠረ - የአሜሪካ የባህር ኃይል
ኢራን በህገወጥ መንገድ ዘይት ያጓጉዛሉ የምትላቸውን ታንከሮች አዘውትረው ትይዛለች
ከዓለማችን አንድ አምስተኛው ዘይት በኢራንና ኦማን መካከል ባለው ባህር በኩል የሚተላለፍ ነው
የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ሀሙስ እለት በባህረ ሰላጤው ዓለም አቀፍ ውሃ ውስጥ የንግድ መርከብን "በግዳጅ ያዘ" ተብሏል።
መርከቧም በህገ-ወጥ ዝውውር ላይ የተሳተፈች ሳትሆን አትቀርም ሲል የአሜሪካ የባህር ኃይል ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የባህር ኃይል ሁኔታውን ተከታትሎ ምንም አይነት ምላሽ ላለመስጠት ወስኗልም ተብሏል።
ኢራን በበኩሏ በባህረ ሰላጤው ውሃ ላይ ሲጓዙ ከነበሩት ታንከሮች መካከል አንዱ ከኢራን መርከብ ጋር በመጋጨቱ ለመያዝ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳላት ገልጻለች።
የብሪታንያ የባህር ላይ ደህንነት ኩባንያም አንዲት ትንሽ የታንዛኒያ ጀልባ የኢራን ኃይሎች ለመያዝ ሙከራ ማድረጋቸውን ተናግሯል።
"ኢራን በህገወጥ መንገድ ዘይት ያጓጉዛሉ ብላ የጠረጠራቸውን ትናንሽ ታንከሮች አዘውትሯ ትይዛለች" ሲል ኩባንያው አክሎ ተናግሯል።
ከዓለማችን አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ዘይትና የዘይት ምርቶች በኢራን እና ኦማን መካከል ባለው የሆርሙዝ ባህር በኩል ይተላለፋል።
የአሜሪካ የባህር ኃይል ኢራን በኦማን ባህረ ሰላጤ ላይ ሁለት የንግድ ታንከሮችን እንዳትይዝ ጣልቃ መግባቱን ገልጿል።
ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ በአካባቢው መርከቦች ላይ ተከታታይ ጥቃቶች ይደርሳሉ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።