የሁለቱ ሀገራት አለመስማማት በየመን፣ በሶሪያ እና ሊባኖስ አሉታዊ የሆነ ተጽእኖ ሲያሳድር ቆይቷል
ኢራን በሳኡዲ አረቢያ የሚገኘውን ኢምባሲዋን ከሰባት አመታት በኋላ ከፈተች።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማደስ እና በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ይፈጥር የነበረውን ተቀናቃኝነታቸውን ለማርገብ መስማማታቸውን ተከትሎ ነው ኢራን ኢምባሲዋን የከፈተች።
ኢራን ለሰባት አመታት ተዘግቶ የነበረውን በሳኡዲ አረቢያ የሚገኘውን ኢምባሲዋን መክፈቷን ሮይተርስ ዘግቧል።
በመክፈቻ ስነ ስርአቱ ወቅት በርካታ ባለስልጣናት እና ዲፕሎማቶች ተገኝተው እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል።
የኢራን የቆንሳል ጉዳዮች ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊረዛ ቢከድሊ"የዛሬውን ቀን በኢራን እና በሳኡዲ አረቢያ ግንኙነት ወሳኝ ቀን አድርገን እንወስደዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ቀጣናው ወደተሻለ ትብብር እና ብልጽግና ያመራል ሲሉም ተናግረዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር በቻይና አደራዳሪነት ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ ለአመታት የዘለቀውን ቅራኔ የሚቋጭ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሀገራት አለመስማማት በየመን፣ በሶሪያ እና ሊባኖስ አሉታዊ የሆነ ተጽእኖ ሲያሳድር ቆይቷል።
የተደረሰው ስምምነትም ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ተጽእኖ ያሳየ ነበር።
ሳኡዲ አረቢያ በኢራን የሚገኘውን ኢምባሲዋን የዘገችው በፈረንጆቹ 2016 በኢምባሲዋ ላይ ጥቃት በመድረሱን ተከትሎ ነበር።