መርከቡ የባህር ላይ ጥቃት ማድረስ እና ማክሸፍ የሚችል ሚሳኤል ይታጠቃል ተብሏል
ኢራን አዲስ የጦር መርከቧን ሀይፐርሶኒክ ሚሳኤል እንደምታስታጥቅ ገለጸች።
የመካከለኛ ምስራቋ ሀገር ኢራን አዲስ የጦር መርከብ መስራቷን አስታውቃለች።
ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ጋር ግጭት ውስጥ ያለችው ኢራን ግዙፍ ወታደራዊ መርከቧን ለዓለም አስተዋውቃለች።
ይህ አዲስ የውጊያ መርከብ ዳማቫንድ-2 የተሰኘ ሲሆን በቅርቡ ለዓለም ያስተዋወቀችውን ሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤልን ይታጠቃል ብላለች።
የኢራን ባህር ሀይል አዛዥ ሪር አድሚራል ሻህራም ኢራኒ እንዳሉት አዲሱ የጦር መርከብ የሚሰነዘሩ የሚሳኤል ጥቃትን ማክሸፍ እና ጥቃት ማድረስ የሚያስችሉ ሚሳኤሎችን ይታጠቃል ማለታቸውን አርቲ ዘግቧል።
አዲሱ የጦር መርከብ በሰሜናዊ ኢራን በካስፒያን ባህር በኩል እንደሚሰማራም ተገልጿል።
ኢራን ተጨማሪ የጦር መርኩብ በመስራት ላይ መሆኗን የተናገሩት የባህር ሀይል አዛዡ ቴህራን በጠላቶቿ የምትፈራ ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ግጭት ውስጥ ያለችው ኢራን ከምንግዜም ተቀናቃኟ ሳውዲ አረቢያ ጋር የነበራትን የሻከረ ግንኙነት አድሳለች።
በቻይና አደራዳሪነት ከሪያድ ጋር ጥሩ ግንኙነት የመሰረተችው ኢራን ከቀናት በፊት የሻንጋይ ትብብር ቡድንን በይፋ ተቀላቅላለች።
ኢራን ከሻንጋይ ትብብር ቡድን ባለፈም ብሪክስን ለመቀላቀል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሆነች የተገለጸ ሲሆን የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ በይፋ አባል መሆኗ እንደሚታወቅ ይጠበቃል ተብሏል።