ኢራን በአደባባይ አመፅ ተሳትፈዋል ያለቻቸውን ግለሰቦች በሞትና በእስራት መቅጣቷ ተገለጸ
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በትናንትናው እለት በዋለው ችሎት ግለሰቦቹ በሞትና በእስራት እንዲቀጡ ወስኗል
በሞት እንዲቀጣ የተወሰነበት ስሙ ያልተጠቀሰ ኢራናዊ "መንግስትን በአመፅ የመገልበጥ" በሚል ነው የተከሰሰው
የኢራን ፍርድ ቤት በአደባባይ አመፅ ተሳትፈዋል በሚል የተከሰሱ ግለሰቦች በሞትና በእስራት እንዲቀጡ ወሰኑ።
በዚህም የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በትናንትናው እለት በዋለው ችሎት አንድ ግለሰብን በሞት ሌሎች አምስት በአመፁ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉትን ደግሞ ከ5 እከ 10 አመት እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
በሞት እንዲቀጣ የተወሰነበት ስሙ ያልተጠቀሰ ኢራናዊ "መንግስትን በአመፅ የመገልበጥ" ክስ ቀርቦበታል።
የህዝብን ሰላምና መረጋጋት ማደፍረስ፣ የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ መጣልና የሙስና ክሶች እንደቀረቡበት ነው የኢራን ብሄራዊ የዜና ወኪል ኢርና የዘገበው።
ግለሰቡ በመዲናዋ ቴህራን በመንግስት ተቋም ላይ እሳት በመለኮስ አመፁን ለማቀጣጠል መሞከሩም ተገልጿል።
አምስቱ ግለሰቦች "በመብሰብና የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነትና የህዝብ ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል በመደራጀት ወንጀል" ተከሰው ነው በቴህራን የሚገኘው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያሳለፈባቸው።
የትናንቱ የሞትና የእስራት ውሳኔ ይግባኝ ሊጠየቅበት ይችላል ተብሏል።
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረችው የ22 አመቷ ማህሳ አሚኒ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቷ ማለፉ ከተነገረ በኋላ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የሚወጡ ኢራናውያን ተበራክተዋል።
ተቃውሞው ከጀመረ ወዲህ ከ300 በላይ ሰዎች በፀጥታ ሃይሎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
የትናንቱ ውሳኔም የአደባባይ ተቃዋሚዎችን ለማስጠንቀቅ ያለመ ስለመሆኑ ነው የተገለፀው።