የፖለቲካ ባላንጣዎቹ አሜሪካ እና ኢራን በኳታሩ የአለም ዋንጫ በአንድ ምድብ ይፋለማሉ
እንግሊዝ እና ዌልስ በሚገኙበት ምድብ የተደለደሉት ሁለቱ ሀገራት ሁለተኛውን ፖለቲካ የተጫነው የአለም ዋንጫ ፍልሚያ ያደርጋሉ
ኢራን በአለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኳ አሜሪካን በማሸነፍ ነው የመጀመሪያ ድሏን ያስመዘገበችው
በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ከምዕራባውያን ጋር የምትነታረከው ኢራን በኳታሩ የአለም ዋንጫ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።
በምድብ 2 ከእንግሊዝ እና ዌልስ ጋር የተደለደሉት አሜሪካ እና ኢራን ሚያደርጉት ጨዋታ ከእግር ኳስም በላይ ነው።
የ1979ኙ የኢራን አብዮት ከአሜሪካ ጋር መልካም ወዳጅነት የነበራቸውን ሽህ ሞሃመድ ሬዛ ፓህላቪ ካስወገደ ወዲህ የአሜሪካ እና የኢራን ግንኙነት መሻከር ጀምሯል።
በአያቶላህ ሮሁላህ ሆሚኒ የሚተላለፉ ጸረ አሜሪካ መልዕክቶችም ፖለቲካዊ ውጥረቱን እያናሩት መጡ። ከአብዮቱ 19 አመት በኋላ በ1998 ፈረንሳይ ባስተናገደችው የአለም ዋንጫም ይሄው የሃገራቱ ጸብ በጉልህ ተንጸባረቀ።
ባላንጣዎቹ ሰላምና ወንድማማችነትን በሚሰብከው የአለም ዋንጫ እርስ በርስ ሊጫወቱ መሆኑ ሲገለጽ ከየአቅጣጫው የስጋት አስተያየቶች ይሰጡ ጀመር።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪው ሆሚኒ በወቅቱ የአሜሪካውያን ተጫዋቾች እጅ እንዳትጨብጡ ማለታቸውም በተጠባቂው ጨዋታ ላይ ጥላ አጠላበት።
ከ7 ሺ በላይ ትኬቶች ተቃውሞ ለማስነሳት ባሰቡ ደጋፊዎች እጅ መግባቱ ከተነገረ በኋላም የፈረንሳይ የደህንነት ሰራተኞች ካሜራ ጠምደው በፖለቲካ የተወጠረውን ጨዋታ ለማርገብ ይጠባበቁ ያዙ።
የተፈራውን አመጽ ግን የአሜሪካ እና ኢራን ተጫዋቾች በጋራ ፎቶግራፍ ሲነሱ ረገበ።
የፐርሽያ አናብስቶች 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸውም ከሊዮን እስከ ቴህራን ኢራናውያንን በደስታ እምባ አራጨ። ጨዋታው በአለም ዋንጫ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያረበበት አስፈሪ ፍልሚያ ሆኖ ከመመዝገብ ግን አልዳነም።
በመካከለኛው ምስራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተስተናደው የኳታሩ የአለም ዋንጫም ሀገራቱን በአንድ ምድብ ሲያገናኝ የ1998ቱ ክስተት ይደገም ይሆን የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
አሜሪካ እና ኢራን በምድብ 2 ከእንግሊዝ እና ዌልስ ጋር ተደልድለዋል።
ኢራን በኳታር 6ኛ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ነው የምታደርገው። ከአለም ሀገራት 20ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የፐርሽያ አናብስት ከምድባቸው አልፈው ግን አያውቁም።
የድል ሪከርዳቸውም ሁለት ጊዜ ነው፥ በ1998 አሜሪካን 2 ለ 1 ያሸነፉበትና ከ4 አመት በፊት በሩስያ ሞሮኮን 1 ለ 0 የረቱበት።
ክሮሽያዊው ድራጋን ስኮቺች የሚያሰለጥኑት የኢራን ብሄራዊ ቡድን በተፈጥሮ ድንቅ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችን የያዘ ነው።
ባለፈው አመት ከዘኒት ሴንት ፒተርስበርግ ወደ ጀርመኑ ባየር ሊቨርኩስን የተዛወረው ሳርዳር አዝሙንም የቡድኑ የፊት ደጀን ይሆናል ተብሏል።
አዝሙን ለብሄራዊ ቡድኑ 65 ጊዜ ተሰልፎ 41 ጎሎችን አስቆጥሯል። በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ወጣት ተጫዋቾችም ቡድኑን ተቀላቅለዋል ነው የተባለው።
የተጋጣሚያቸው የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድንም በግረግ በርሃልተር እየተመራ የ1998ቱን ሽንፈት በድል ለመመለስ መዘጋጀቱ እየተነገረ ነው።
በፈረንጆቹ ህዳር 29 በአል ቱማምማ ስታዲየም ከኢራን ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ የ24 አመቱ ክርስቲያን ፑሊሲች ትልቅ ሃላፊነት ተጥሎበታል።
አሜሪካ በፈረንጆቹ 1930 በኡራጓይ በተጀመረው የአለም ዋንጫ አንስቶ በተሳትፎ ደረጃ ጥሩ ሪከርድ ቢኖራትም (11 ጊዜ) አንድም ጊዜ የአለም ዋንጫ አላነሳችም።
በኳታሩ የአለም ዋንጫም የምድብ ተፋላሚዎቿ የቀደመ ታሪኳን እንድታሻሽል እድል የሚሰጡዋት አይመስልም። ሃሪ ኬን እና ጋሬዝ ቤል የሚመሯቸው እንግሊዝ እና ዌልስ ከምድቡ ለማለፍ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።
በጋሬት ሳውዝጌት የምትሰለጥነው እንግሊዝ በአለም የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ 5ኛ ላይ ተቀምጣለች፤ አንድ ጊዜም ዋንጫውን አንስታለች። ሶስቱ አናብስት ከምድብ 2 የማለፍ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
ከ1958 በኋላ ሁለተኛው የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን የምትደርገው ዌልስም ብርቱ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።
የፖለቲካ ውጥረት የሚጎላበት የአሜሪካ እና ኢራን ግጥሚያ ምን ያስመለክተን ይሆን?