የኢራን መንግስት ቴሌቭዥን በቀጥታ ስርጭት ላይ ሳለ በተቃዋሚዎች ተጠልፎ እንደነበር ተገለጸ
ጠላፊዎቹ የኢራኑ ታላቁ መሪ ጭንቅላት በሽጉጥ ኢላማ ሲደረግና ምስላቸው በእሳት ነበልባል ሲያዝ አሳይተዋል
ድርጊቱን የፈጸመው ራሱን “አዳላት አሊ” ወይም “አሊ ዳኛ” ብሎ የሚጣራው የአክቲቪስቶች ቡድን መሆኑ ታውቋል
የኢራን መንግስት ቴሌቭዥን በቀጥታ ስርጭት ላይ ሳለ በጸረ-መንግስት ተቃዋሚዎች ተጠልፎ እንደነበር ተገለጸ፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው የተጠለፈው በማህሳ አሚኒ ሞት ምክንያት ባገረሸው ተቃውሞ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ሶስት ሰዎች በጥይት ከተገደሉ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
የተቃዋሚዎቹ ቴሌቭዥኑን ስርጭት ከጠለፉ በኋላ በመተላለፍ ላይ የነበረውን ዜና በማቋረጥ በሀገሪቱ መሪ ላይ የተነሳው ተቃውሞ የሚያሳዩ ምስሎች ማስተላለፋቸው ተገልጿል፡፡
ከበስተጀርባ በሙዚቃ በታጀበው ተቃውሞ “ጂን ፣ጂያን ፣አዛዲ” - ትርጉሙ “ሴት ፣ህይወት ፣ነጻነት” የሚል መፈክር ሲሰማ እንደነበርም ኢራን ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡
ቀጥሎም በስክሪኑ ላይ ጭንብል ከታየ በኋላ የኢራኑ ታላቁ መሪ አሊ ካሜኒ ጭንቅላታቸው በሽጉጥ ኢላማ ሲደረግና ምስላቸው በእሳት ነበልባል ሲያዝ አሳይቷል።
ለጥቂት ሴኮንዶች በቆየው የጠለፋ ድረጊት የማህሳና በቅርብ በነበረው ተቃውሞ የተገደሉ ሶስት ሴቶችንም ምስሎች የተላለፉበት እንደነበርም ተገልጸዋል፡፡
በፎቶው ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች አንዱ “ተቀላቀሉን እና ተነሱ” የሚሉ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “የወጣቶቻችን ደም ከመዳፋችሁ ላይ ይንጠባጠባል” የሚሉ ናቸው።
ድረጊቱ የፈጸመው ራሱን “አዳላት አሊ” ወይም “አሊ ዳኛ” ተብሎ የሚታወቀው የአክቲቪስቶች ቡድን ነው፡፡
ለጠላፋው ኃላፊነት እንደሚወስድ በግልጽ ያስታወቀው ቡድኑ፤ ጠለፋውን “ጣፋጭ ወቅት” በማለት የቲዊተር ተጠቃሚዎች የጠለፋውን ምርጥ ትውስታ እንዲልኩ አበረታቷል።
የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ነው።
የማህሳ አሚኒ ሞት ታዲያ በኢራን ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ማዕበል ቀስቅሷል።
በኢራን ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደረገው የሚታዩት አያቶላ አሊ ካሜኒ እንደዚህ አይነት ተቃውሞ ሲገጥማቸው በኢራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡ በኢራን ተቃውሞ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ150 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች ተናግረዋል።