ዩክሬን ላቀረበችው ክስ መረጃ ካላት ይፋ ታድርግ ስትል ኢራን አስታውቃለች
ኢራን ለሩሲያ ድሮን ሰጥታለች በሚል የቀረበባትን ክስ ውድቅ አደረገች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት
ካመራች ሰባተኛ ወራቸው ላይ ይገኛሉ፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ የደረሰባትን ጥቃት ለመመከት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት የጦር መሳሪያ ፣ የወታደራዊ መረጃዎች እና የገንዘብ ድጋፎችን እያገኘች ትገኛለች፡፡
ዩክሬን በተደረገላት ድጋፍም ከዚህ በፊት በሩሲያ ጦር ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መልሳ በማስለቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ ከኢራን በተደረገላት የሰው አልባ ጦር መሳሪያ ወይም ድሮን የዩክሬን ወታደሮች ላይ አዲስ ጥቃት እየተሰነዘረ ነው ስትል ቴህራንን ከሳለች፡፡
ኢራን ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አድርጋለች በሚልም በኬቭ ባለው የኢራን ኢምባሲ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች ቁጥርን ገድባለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኢራን በበኩሏ የዩክሬን ክስ ሀሰት እና በመረጃ ያልተደገፈ ነው በሚል ውድቅ ያደረገች ሲሆን በዲፕሎማቶች ቁጥር ላይ የወሰነችውም ውሳኔ የችኮላ ነው ብላለች፡፡
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ እንዳሉት ዩክሬን ኢራን ድሮን ለሩሲያ ሰጥታለች ከማለቷ በፊት መረጃዋን ይፋ ልታደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ዩክሬን በኢራን ላይ ክስ ልታቀርብ የቻለችው የቴህራን ወዳጅ ባልሆኑ ምዕራባዊያን ሀገራት ግፊት ነው፡፡
ኢራን ዩክሬን ለወሰደችው እርምጃም ተመጣጣኝ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ በቃል አቀባዩ በኩል አስታውቃለች፡፡
በደቡባዊ ዩክሬን ያሉ ወታደራዊ አዛዦች በበኩላቸው ሰባት ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖችን መተን ጥለናል ብለዋል፡፡