የኢራንና ቱርክ ፕሬዝዳንቶች በጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ በአንካራ ተወያዩ
መሪዎቹ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አድማሱን እያሰፋ እንዳይሄድ በሚያስችሉ ጉዳዮች መምከራቸው ተገልጿል
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ደጋግማ ያወገዘችው አንካራ ከቴል አቪቭ ጋር የንግድ ግንኙነቷን አለማቋረጧ በቴህራን ተቃውሞ ገጥሞታል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ለይፋዊ ጉብኝት ቱርክ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ራይሲ በቱርክ ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት ለሁለት ጊዜ ተራዞ ዛሬ አንካራ የገቡ ሲሆን ከቱርክ አቻቸው ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር ተወያይተዋል።
የውይይታቸው ዋነኛ አጀንዳም ሶስት ወራት ያለፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት መሆኑን የቱርክ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የእስራኤል እና ፍልስጤም የአስርት አመታት ጦርነት ሁለት ሀገር መፍትሄ ወይም “ቱ ስቴት ሶሊዩሽን” እንዲፈታ ድጋፍ ታደርጋለች፤ ቴል አቪቭ ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ በፍልስጤማውያን ላይ የምትወስደውን እርምጃም ደጋግማ ተቃውማለች።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን “አሸባሪው ኔታንያሁ እንጂ ሃማስ አይደለም፤ ኔታንያሁ በጦር ወንጀል መጠየቁ አይቀርም” የሚሉና ሌሎች ጠንከር ያሉ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውንም ሬውተርስ አስታውሷል።
እንደ ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት ሃማስን በሽብርተኛ ቡድንነት ያልፈረጀችው አንካራ፥ በቴል አቪቭ ላይ የተጀመረው የዘር ማጥፋት ክስን እንደምትደግፍ መግለጿም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ እስካሁን ከእስራኤል ጋር የንግድ ግንኙነቷን አለማቋረጧ የፍልስጤማውያንን የነጻነት ትግል በሚደግፉት እንደ ኢራን ባሉ ሀገራት ተቃውሞ ገጥሞታል።
ሃማስን ጨምሮ የሊባኖሱን ሄዝቦላህ፤ የየመኑን ሃውቲ ታጣቂ ቡድን ትደግፋለች የምትባለው ኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በዛሬው ውይይት ይሄንኑ ጉዳይ ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው የተዋጉት ቱርክና ኢራን ግንኙነታቸውን በማደስ ላይ ይገኛሉ።
ኢራን እና ፓኪስታን ባለፈው ሳምንት የገቡበትን ፍጥጫ ለማርገብም ቱርክ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ ነው የተነገረው።
በአንካራ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ከኤርዶሃን ጋር የሀገራቱን የንግድ ግንኙነት (በተለይ በተፈጥሮ ጋዝ ነዳጅ) ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች መነጋገራቸው ተዘግቧል።