ለጋዛ የቃላት ጋጋታ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ድጋፍ ያስፈልጋል - ኢራን
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ የአረብና ሙስሊም ሀገራት ለጋዛ በህብረት የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል
ፕሬዝዳንቱ በሳኡዲ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ጉዞ ጀምረዋል
በጋዛ እየተካሄደ ለሚገኘው ጦርነት ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥበት ወቅት አሁን ነው አሉ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ።
ፕሬዝዳንቱ በቴህራን አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ፥ ጋዛ የቃላት ጋጋታ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ድጋፍን ትሻለች ሲሉ ተደምጠዋል።
“የአረብና ሙስሊም ሀገራት አንድነት በዚህ ወቅት ወሳኝ ነው” ያሉት ራይሲ፥ ሀገራት በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን ውድመት ከማውገዝና ተኩስ እንዲቆም ከመጠየቅ የተሻገረ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
“አሜሪካ ጦርነቱ እንዳይስፋፋ ፍላጎት እንዳላት ትገልጻለች፤ ለኢራንና ለተለያዩ ሀገራትም መልዕክት ትልካለች፤ ይሁን እንጂ በተግባር እየፈጸመች ያለችው ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ዋሽንግተን በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረግ ማገዷን በመጥቀስም ጦርነቱን እየመራች ያለችው አሜሪካ ናት ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
“አለም ትክክለኛውን የአሜሪካ መልክ (ገጽ) ማየት አለበት” ያሉት የኢራኑ ፕሬዝዳንት፥ ለፍልስጤማውያን ፈጥነን እንድረስላቸው የሚል ጥሪንም አቅርበዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሳኡዲ ባዘጋጀችውና በጋዛ ሰላምን ለማስፈን ባለመው የአረብና ሙስሊም ሀገራት ጉባኤ ይሳተፋሉ።
ሪያድ እና ቴህራን በመጋቢት ወር 2023 ግንኙነታቸውን ለማደስ መስማማታቸው የሚታወስ ነው።
ራይሲ በሳኡዲ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ለማድረግም ጉዞ መጀመራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።
ሪያድ ባዘጋጀችው የአረብና ሙስሊም ሀገራት ጉባኤ የሚታደሙት ፕሬዝዳንት ራይሲ ዛሬ በቴህራን አውሮፕላን ማረፊያ የሰጡትን መግለጫ ደግመው ያስተላልፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የፍልስጤሙን ሃማስ እና የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ትደግፋለች የምትባለው ኢራን የአሜሪካ ጣልቃገብነት ካልቆመ ቀጠናው ወደባሰ ውጥረት ውስጥ እንደሚገባ ስታሳስብ ቆይታለች።
በዛሬው እለት የሚካሄደው ጉባኤም የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በጋዛ ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም እንዲይዙ ቴህራን ጥሪ የምታቀርብበት እንደሚሆን ተገልጿል።