ኢራን ሂጃብ የማይለብሱ ሴቶችን በ10 ዓመት እስራት ልትቀጣ ነው
የሀገሪቱ ም/ቤት የአልባሳት ደንብን የማይከተሉ ሴቶችን ቅጣትን ከፍ የሚያደርግ አወዛጋቢ አዋጅ አጽድቋል
ኢራን ባለፈው ዓመት በአለባበስ ክልከላ ከባድ ተቃውሞ ገጥሟታል
ኢራናዊያን ሴቶች "አግባብ ያልሆነ አልባሳት" ለብሰው ከተገኙ የ10 ዓመት እስራት ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
የሀገሪቱ ምክር ቤት የአልባሳት ደንብን የማይከተሉ ልጃገረዶችንና ሴቶችን የእስራት ጊዜና ቅጣትን ከፍ የሚያደርግ አወዛጋቢ አዋጅ አጽድቋል።
በአዋጁ ያላግባብ የለበሱ የተባሉ ሴቶች እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣሉ። የፍርድ ቤት ሂደቱም እስከ ሦስት ዓመት ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
ረቡዕ የጸደቀው አዋጅ በህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ያለአግባብ የሚለብሱ ሴቶች በሀገሪቱ ወንጀል ህግ መሰረት አራተኛ ደረጃ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
በዚህም እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራትና ከሦስት ሽህ እስከ ሰባት ሽህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ሆኖም አዋጁ ህግ እንዱሆን በጠባቂዎች ምክር ቤት መጽደቅ ይጠበቅበታል።
እርምጃው ማሻ አሚኒ የተባለች ሴት በፖሊስ ጥበቃ እያለች ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በሀገሪቱ ከባድ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ከዓመት በኋላ የተወሰደ ነው።
በተቃውሞው ሴቶች ሂጃባቸውን በማቃጠልና በመወርወር መንግስትን አሻፈረኝ ብለዋል።