ፖለቲካ
የኢራን ዩኒቨርሲቲዎች የምናስተምረው "የተሸፈኑ" ሴቶችን ብቻ ነው አሉ
የሀገሪቱ ሳይንስ ሚኒስቴር ሙሉ ለሙሉ ሂጃብ የማይለብሱ ሴት ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎት እንደማያገኙ ገልጿል
በሀገሪቱ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወዲህ ሂጃባቸውን የሚያወልቁ ሴቶችና ልጃገረዶች ቁጥር ከፍ እያለ መሄዱ ተነግሯል
ኢራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መማር የሚፈልጉ ሴት ተማሪዎች ሂጃብ የመልበስ ግዴታ አለባቸው አለች።
የሀገሪቱ ሳይንስ ሚንስቴር እንዳስታወቀው በሀገሪቱ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሂጃብ ላልለበሱ ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎት አይሰጥም።
ባለፈው መስከረም በኢራን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ማህሳ አሚኒ በእስር ቤት መሞቷን በመቃወም ሂጃባቸውን ያወለቁ ሴቶች እና ልጃገረዶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ተብሏል።
ሚኒስቴሩ እሁድ እለት በሰጠው ውሳኔ በተቋሙ ቁጥጥር ስር ያሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና የከፍተኛ ትምህርት ማዕከላት ህጉን ለማያከብሩ ተማሪዎች ትምህርታዊ አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ መከልከሉን ተናግሯል።
በሁሉም የኢራን አካባቢዎች የሚገኙ የህክምና ሳይንስ ዩኒቨርስቲዎች አገልግሎታቸውን እንደሚከለክሉም ገልጸዋል።
ሙሉ ለሙሉ ሂጃብ አድርገው ለመሸፈን ቁርጠኝነት የሌላቸው ሴት ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎት አያገኙም ነው የተባለው።
የኢራን ፓርላማ አባላት የግዴታ መሸፈንን በማይከተሉ ሴቶች ላይ ተጨማሪ ቅጣት እንዲጣል ሀሳብ ማቅረባቸውም ተገልጿል።