ኢራንን ያስቆጣው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ንግግር ምንድን ነው?
የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ንግግር የሀገራቱን ግንኙነት በማሻከር ቴህራንና ሴዑል አምባሳደሮቻቸውን እስከመጥራት ደርሰዋል
የደቡብ ኮሪያ ባንኮች የቴህራንን 7 ቢሊየን ዶላር አለመመለሳቸው ግንኙነታቸውን አሻክሮት ቆይቷል
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ኢራንን በተመለከተ ያረጉት ንግግር የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ሻክሯል።
በኤምሬትስ ከሰሞኑ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ዮን በአቡዳቢ ከሚገኙ የሀገራቸው ወታደሮች ጋር ሲመክሩ ሴኡልና አቡዳቢ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
ለደቡብ ኮሪያ ጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ፤ ለአረብ ኤምሬትስ ደግሞ ኢራን "ቀንደኛ ጠላትና የደህንነት አደጋ" ናቸውም ነው ያሉት።
ሁለቱም ሀገራት በሴኡል እና ቴህራን የሚገኙ አምባሳደሮቻቸውን መጥራታቸው ተገልጿል
ኢራን ከሰሜን ኮሪያ ጋር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ፈፅማለች በሚል ደቡብ ኮሪያ የቴህራንን ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ካገደች በኋላ የሀገራቱ ግንኙነት መሻከር ጀምሯል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት በአቡ ዳቢ ያደረጉት ንግግርም ይበልጥ ወጥረቱን ጨምሮት ቴህራን በሴኡል የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች።
ጉዳዩ በንግግር ካልተፈታም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ አደጋ ላይ ይወድቃል ስትል አስጠንቅቃለች ብሏል የሀገሪቱ የዜና ወኪል ኢርና።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትሩ ሬዛ ናጃፊ፥ የፕሬዝዳንት ዮን ንግግርን "ጣልቃገብነት" ነው፤ በቀጠናውም ሰላምና መረጋጋትን የሚያሰፍን አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የናጃፊ አስተያየትም ሴኡልን አስቀይሞ የኢራኑን አምባሳደር ለማብራሪያ መጥራቷ ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ፅህፈት ቤት በበኩሉ፥ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የደቡብ ኮሪያ ወታደሮችን ሞራል ከፍ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ ነው ያስታወቀው።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለቴህራን ተደጋጋሚ ማብራሪያዎችን መሰጠቱን መግለፁን ሬውተርስ አስነብቧል።
ኢራን የአሜሪካ ማዕቀብን ተከትሎ በደቡብ ኮሪያ ባንኮች የተያዘባት 7 ቢሊየን ዶላር እንዲለቀቅላት በተደጋጋሚ ብትጠይቅም እስካሁን አልተመለሰላትም።